Skip to content
Newsroom

ለትምህርትና ስልጠና አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት የዋና ክህሎቶች (Core Skills) ስልጠና ተሰጠ

ETA Education & Training Authority November 13, 2026 1 min read
ለትምህርትና ስልጠና አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት የዋና ክህሎቶች (Core Skills) ስልጠና ተሰጠ

ለትምህርትና ስልጠና አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት የዋና ክህሎቶች (Core Skills) ስልጠና ተሰጠ

የኢፊዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ለትምህርትና ስልጠና አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ከህዳር 1 እስከ 4 ቀን 2019 ዓ.ም አዳማ ከተማ በሚገኘው መልካ አዳማ ሆቴል የዋና ክህሎቶች (Core Skills) ስልጠና ሰጠ ።
በስልጠና መረሀ ግብሩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ታደሰ እንዳሉት ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1263/14 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 515/2014 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የትምህርትና ስልጠና ጥራት ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል የከፍተኛና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ፤የእውቅና አሰጣጥ ፤የከፍተኛ ትምህርት የፈቃድ አሰጣጥና እድሳት፤የጥራት ኦዲት እና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥና የአቻ ግመታ ፤ የዓለም አቀፍና የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች የፈቃድ አሰጣጥና እድሳት መሆኑን ገልጸው ባለሥልጣኑ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለማከናወን የአጋር ድርጅቶች እና የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ተጠባባቂ መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ሙሉ ገ/ኪዳን በበኩላቸው በባለሥልጣኑ የሚከናወኑ ሥራዎችን በብቃት ለማከናወን እንዲቻል የሥራ ክፍላቸው አቅዶ ፤የአጋር አካላትን ትብብር ጠይቆ እና ፈጣን ምላሽ አግኝቶ ስልጠናው እንዲካሄድ ማድረጉን ገልጸው ለዚህም የዓለም የሥራ ድርጅትን (ILO) አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም እንደዚህ ዓይነት መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት የሥራ ክፍሉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት ዓለም የስራ ድርጅት (ILO) ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ዘውዴ ለአራት ቀናት በሰጡት ስልጠና የማህበራዊ፣ የአእምሮ ማስተዋል እና የስሜት ብስለት (Emotional Intelligence) ክህሎቶች፤ራስን የማስተማር እና ራስን የመምራት ብቃት፤ ውጤታማ የሥራ ላይ ተግባቦት እና የግጭት አስተዳደር፤ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እና የአረንጓዴ ሥራዎች (Green Jobs) ጽንሰ-ሀሳብ እና መሠረታዊ ክህሎቶችን በዕለት ተዕለት ሥራ ላይ የማስረጽ ስልቶች ላይ ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ አድረገዋል ፡፡
በመርሃ-ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የባለሥልጣኑ የቴክኒክና ሙያ የትምህርትና ስልጠና የዴስክ ኃላፊ እና የስልጠና መረሀ-ግብሩ አስተባባሪ አቶ ግሩም መኮንን በበኩላቸው ስልጠናው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን በብቃት ለመምራት፤ የገቢያ ፍላጎትን በመረዳት የሰልጣኞችን የሥራ እድል ለማስፋት፤የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ከኢንዱስትሪ ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር፤ ችግሮችን ለመፍታት፤ውጤታማ ተግባቦት ለማድረግ እና የለውጥ ቴክኖሎጂን በመቀበል ዲጂታል ክህሎት ለማዳበር ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ግሩም የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ሲከናወን ገንቢ ግብረ መልስ ለመስጠት፤ተቋማትን በመግባባትና መፍትሄ ባለው አግባብ ለመከታተል፤በአሰራር ሂደት ሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ መልኩ ለመፍታት፤ስልታዊ ውሳኔ ለመስጠት፤ተቋማዊ ባህልን ለማሻሻል፤ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እና የጥራት ባህልን ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን
በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA
በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA
በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA
በዌብሳይት www. neta.gov.et ይከታተሉ ።

Gallery

News Announcement
Share