Skip to content
Newsroom

በባለሥልጣኑ ISO 9001/2015 የጥራት አመራር ሥርዓት ትግበራ በይፋ ተጀመረ

ETA Education & Training Authority October 11, 2026 1 min read
በባለሥልጣኑ ISO 9001/2015 የጥራት አመራር ሥርዓት ትግበራ በይፋ ተጀመረ

በባለሥልጣኑ ISO 9001/2015 የጥራት አመራር ሥርዓት ትግበራ በይፋ ተጀመረ
መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የISO 9001/2015 የጥራት አመራር ሥርዓት ትግበራ ይፋዊ ማስጀመሪያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መረሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመረሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለሥልጣኑ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ መስፍን  እንዳሉት  ባለሥልጣኑ ከ2015ዓ.ም ጀምሮ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን እና በርካታ የአደረጃጀት እና የአሰራር ለውጦች ማድረጉን በዚህም ጉልህ ሚና ያላቸው ሥራዎች ሲያከናወን መቆየቱን ገልጸው ሥራዎቻችንን በአግባቡ ለመምራት እና  ህብረተሰቡ በባለሥልጣኑ ላይ ያለው አመኔታ እንዲያድግ የ ISO 9001/2015 የጥራት አመራር  ሥርዓት ትግበራ  ወሳኝ ሚና ያለውና ታሪክ የማይረሳው በመሆኑ ሁሉም የባለሥልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞች ለትግበራው እንዲረባረቡ አሳስበዋል፡፡
የባለሥልጣኑ የውስጥ ጥራት ኦዲት እና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዝናቡ ሀምሳሉ በበኩላቸው  የባለሥልጣኑን የማኔጅመንት ውሳኔ ተከትሎ ባለፉት  ስድስት ወራት ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ ስምምነት ተደርጎ ፤ ግብረሀይል ተቋቁሞ እና ከሌሎች ተቋማት ልምድ ተወስዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
የሥራ ክፍሎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የአሰራር ሰነዶችን  ከጥራት አመራር  ሥርዓቱ ጋር እንዲጣጣሙ  እና አዳዲስ የአሰራር ሥርዓት ሰነዶችም እንዲዘጋጁ በማድረግ የአምስት መቶ ሀምሳ ስድስት  ሰነዶች ዝግጅት መከናወኑን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው የተዘጋጁትን ሰነዶች አጠቃቀም በአግባቡ መረዳት እና ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም  የሥራ ክፍሎች የሚጠበቅ  መሆኑን  ተናግረዋል፡፡
የISO ትግበራ ሥራ ቀጣይነት ያለው መሻሻል የሚያስፈልገው፤በፈቃደኝነት የሚተገበር ፤ የአምራች፣የተቆጣጣሪና የደንበኞች ስምምነት የሚፈልግ፤በየአምስት ዓመቱ የሚከለስ ፤በተቋም፣በሙያ ማኅበራት፣በሀገርና  በዓለም አቀፍ እንዲሁም በዘርፍ ደረጃ  የሚወጡ የጥራት መለኪያ ስታንዳርዶችን የሚያካትት ፤እንደ ንግድ ምልክት የሚቆጠር፤ተአማኒነትን የሚያሳድግ፤ከፍተኛ ጥራትን በትንሽ ወጪ ለማምጣት የሚያስችል፤ዓላማ ተኮር የሆነ ፤የሚያጋጥሙ ስጋቶችንና መልካም አጋጣሚዎችን ታሳቢ ያደረገ እና ቁርጠኝነትን የሚጨምር መሆኑን በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት  የስልጠና እና የቴክኒካል ድጋፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መንግስቱ ተፈራ  በሰጡት የጥራት አመራር ሥርዓት መሠረታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ  አብራርተዋል፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የጥራት አመራር ስርዓት ሰነዶችና መዛግብቶችን ከISO ሰነድ ምእራፎች ጋር ለማገናዘብ እና ለማጣጣም የሚያስችል መሠረታዊ እና በትግበራው ወቅት ሊከናወኑ ሚገባቸው እንዲሁም በትግበራው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች የሚፈቱበትን አግባብ የተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እና ገለጻ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የስልጠና እና የቴክኒካል ድጋፍ ባለሙያ በሆኑት በአቶ አሸናፊ በቀለ ተደርጓል፡፡
ከጥቅምት1ቀን 2019ዓ.ም ጀምሮ የISO 9001/2015 የጥራት አመራር ሥርዓት ትግበራ በይፋ መጀመሩን የሚያሳይ የሰነድ ርክክብ ተደርጎ መረሀ ግብሩ ተፈጽሟል፡፡
የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን
በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA
በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA
በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA
በዌብሳይት www. neta.gov.et ይከታተሉ።

Gallery

News Announcement
Share