የ3ኛ ዙር የጥራት ኦዲተሮች ስልጠና ተሰጠ
በኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የጥራት ኦዲት መሪ ስራ አስፈጻሚ ከመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመለመሉ ሀኪሞች የተቋማዊና የፕሮግራም አካዳሚክ ጥራት ኦዲት የህግ ማዕቀፍ እና መተግበሪያ መሳሪያዎች ላይ ከመስከረም
27-29/2019 ዓ.ም ድረስ አዳማ ከተማ በሚገኘው መልካ አዳማ ሆቴል ስልጠና ሰጠ።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጥራት ኦዲት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትዕግስት ኃ/ስላሴ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በሀገራችን የቁጥጥርና ጥራት የማረጋገጥ ስራ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ባለስልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ተብሎ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ይተገብራቸው ከነበሩት የጥራት ማስጠበቂያ መሳሪያዎች መካከል የአካዳሚክ ጥራት ኦዲት ማከናወን አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሰፊ ቁጥር ባላቸው በግልና በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የጥራት ኦዲት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በሪፎርሙ ሂደትም የጥራት ኦዲት የሕግ ማህቀፎችን፣ ስታንዳርዶችን፣ ውጤት አመላካቾችን እንዲሁም የአሠራር ስርዓት ለማጠናከር ሰፊ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡
ወ/ሮ ትዕግስት እንደገለጹት የጥራት ኦዲት ዲፓርትመንቱ የሕግና የአሠራር ስርዓት ከመዘርጋት ባሻገር ስራው ላይ በቀጥታ የሚሰማሩ ኦዲተሮችን ማሰልጠንና ማብቃት ከአብይ ተግባራቱ መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህም ባለስልጣኑ በ2 ዙር የተቋማዊ አካዳሚክ ጥራት ኦዲተሮችን አሰልጥኖ በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተቋማዊ የአካዳሚክ ጥራት ኦዲት ሥራ ላይ ኦዲተሮችን አሰማርቷል ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ልምዶች በመማር ወደ ፕሮግራም ጥራት ኦዲት እየተሸጋረ መሆኑን የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚዋ የመጀመሪያ ትኩረታችን የሕክምና ኘሮግራም እንዲሆን በማድረግ የዚህ የ3ኛ ዙር ስልጠና ሐኪሞችን ብቻ እንዲያካትት ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ሰልጣኞች ይሄን ስልጠና ሲያጠናቅቁ የተቋማዊና የኘሮግራም ጥራት ኦዲትን ለመተግበር የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎትና የባህሪ ብቃት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ተሳታፊዎች የቅድመ-ስልጠና ፈተና(Pre-training
test) ወስደው በቀጥታ ወደ ስልጠና የገቡ ሲሆን በስልጠናው ቆይታ አጠቃላይ ስለ ባለሥልጣኑ ስልጣንና ተግባር፣ ስለጥራትና ጥራት ማረጋገጥ ጽንሰሀሳብ፣ ስለከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የጥራት ኦዲት መመሪያ፣ የተቋማዊ እና ፕሮግራም አካዳሚክ ጥራት ኦዲት ስታንዳርዶችና ውጤት አመላካቾች፣ የጥራት ኦዲት አሰራር ሂደት(Quality audit procedure)፤ ስለ ግለ-ግምገማ(Self-evaluation)፣ ስለጥራት ኦዲት ሪፖርት አጻጻፍ፤ ስለጥራት ማጎልበቻ እቅድና የክትትል ኦዲት (Enhancement
plan & follow-up audit) እንዲሁም ስለጥራት ኦዲተሮች ምልመላና መረጣ ስልጠና ተሰጥቷዋል።
ስልጠናውን የበለጠ ለማጠናከር በ2018 ዓ.ም የተቋማዊ ጥራት ኦዲት ላይ ከተሳተፉ ኦዲተሮች መካከል ዶ/ር አዱኛ ተመስገን ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና ዶ/ር መላኩ ማስረሻ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በስልጠናው ላይ ተጋብዘው ልምዳቸውን አካለዋል።
ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ሰልጣኞች የድህረ-ስልጠና ፈተና(Post-training
assessment) ከወሰዱ በኋላ የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስነስርዓት ተከናውኗል።
በመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ስራ አስፈጻሚዋ ሰልጣኞች ለ2019 ዓ.ም በተመረጡ ተቋማት የሜዲስን ፕሮግራም ኦዲት ላይ እንደሚሰማሩ ገለጸው ከዚያም ባሻገር በየተቋማቸው በሚደረገው የጥራት ማረጋገጥ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA
በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA
በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA
በዌብሳይት www. neta.gov.et ይከታተሉ።