ሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የምሁራን እና ባለሙያዎች ምክክር ተካሄደ
የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ጥራትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥና የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቱን ይበልጥ ወጥና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ከባለሙያዎች፥ከዘርፉ ተመራማሪዎች እና ምሁራን ጋር ምክክር ተካሄደ።
የምክክር መድረኩ ከነሐሴ 26-28/2018 ዓ.ም አዳማ ከተማ በሚገኘው በመልካ አዳማ ሆቴል የተካሄደ ሲሆን፣ ከተለያዩ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣ ከፌዴራል ስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ቁጥር ባለሥልጣን የተውጣጡ ተመራማሪዎች፣ ምሁራንና የጥራት አረጋጋጭ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የምክክሩ ዋና ዓላማ እና የሦሥት ቀን የቆይታ ዝርዝር መርሃ-ግብ በዶ/ር ሀብታሙ ተሾመ የባለስልጣኑ ስታንደርዳይዜሽንና ብሄራዊ ብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ቀርቧል። ዶ/ር ሀብታሙ በገለጹት መሠረት የምክክሩ ዋና ዓላማ እስከ አሁን ሲከናወን በነበረው በሀገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ጥራት የማረጋገጫ ሂደት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ ከምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ጋር የመጀመሪያውን ምክክር በማካሄድ ብሔራው የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታን ማመቻችት ነው።
በመቀጠል የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው የምክክር መድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የትምህርትና ስልጠና ጥራት የሀገሪቱን የሰው ኃይል ልማት፣ የኢኮኖሚ እድገትና የሀገር ግንባታ ውጤታማነት ከሚወስኑ ዋና ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ ጥራትን ማረጋገጥ የአንድ ተቋም ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም የትምህርትና ስልጠና ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል። ዶ/ር አህመድ በተለይም የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቱ በግልጽ መርሆዎች፣ በተወሰኑ መመዘኛዎችና በተቀናጀ አሠራር ላይ መመሥረት እንዳለበት ገልጸዋል። ለዚህም በሀገሪቱ የሚተገበረውን የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት በማጠናከር የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሚያቀርቡት ትምህርትና ስልጠና የሀገሪቱን ፍላጎትና የሥራ ዓለም ተጠቃሚነት የሚያሟላ እንዲሆን የሚያግዝ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በመድረኩ የባለሥልጣኑ የእውቅናና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዱንካና ንጉሳ ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ጽሑፍ አቅርበዋል። በጽሑፋቸውም ባለሥልጣኑ የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ እስካሁን የሠራቸውን የጥራት ማስጠበቅ ሥራዎች፣ በሂደቱ የታዩ ልምዶችና ክፍተቶች እንዲሁም በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች በስፋት ቀርበዋል።
የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቱ በሀገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ለማሻሻል የሚጫወተውን ሚና በማጠናከር የተማሪዎችና የሰልጣኞች ብቃት፣ የተቋማት አፈጻጸም እና ከሥራ ዓለም ጋር ያለው ትስስር እንዲሻሻል ማድረግ ከሚጠበቁት ዋና ተግባራት መካከል መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።
ጽሑፉ ከቀረበ በኋላ የመድረኩ ተሳታፊዎች በቀረቡት ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን፣ ምልከታዎችንና የመፍትሔ ሃሳቦችን አንስተዋል። ተሳታፊዎቹ በተለይም የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቱ በተግባር ሲተገበር የሚያጋጥሙ ችግሮች፣ የተቋማት የጥራት ደረጃ አመዳደብ፣ የጥራት መለኪያዎች ግልጽነት፣ የተቋማት ተጠያቂነትና የባለድርሻ አካላት ሚና የመሳሰሉ ጉዳዮችን አንስተዋል።
ለተሳታፊዎቹ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው እና ም/ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ዱንካና ንጉሳ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። የተነሱት ሃሳቦችም በማዕቀፉ ዝግጅት ወቅት በጥንቃቄ እንደሚታዩ ተገልጿል።
ዶ/ር አህመድ በበኩላቸው በምክክሩ የተሳተፉ ምሁራን ባቀረቡት ሙያዊ እውቀት፣ ልምድና ምልከታ ለሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፉ ዝግጅት ጠቃሚ ግብዓት እንደሚገኝ ገልጸዋል። ምሁራንና ባለሙያዎች በተግባራዊ ልምዳቸውና በሙያዊ እውቀታቸው ላይ በመመሥረት የሚያቀርቡት ግብዓት ማዕቀፉ ተግባራዊ፣ ዘላቂና የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል።
ከጋራ ውይይቱ በኋላ ተሳታፊዎች በአራት ቡድን ተከፋፍለው ቀድሞ በተዘጋጁ ስምንት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል። ቡድኖቹ በተመደቡላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመወያየት፣ የችግሮችን መነሻ ምክንያቶችና ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመለየት በየቡድኑ የተነሱ ሃሳባቸውን በጋራ መድረክ ላይ አቅርበዋል።
የቡድን ውይይቱም በሁለት ቀናት በስፋት የተካሄደ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ በተለያዩ አቅጣጫዎች የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓቱ እንዴት ሊጠናከር እንደሚችል የራሳቸውን ሙያዊ ሃሳብ አቅርበዋል። በቡድኖቹ የቀረቡት ሃሳቦችም በጋራ ውይይት ተገምግመውና ተጠናክረው ለማዕቀፉ ዝግጅት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ተሰብስበዋል።
በመድረኩ የተነሱት ሃሳቦች እና የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፉን ለማዘጋጀት ጠንካራ መሠረት የጣሉ መሆናቸው ተገልጿል። በተለይም ከተለያዩ የሙያ መስኮች የመጡ ምሁራን የተለያዩ አመለካከቶችን ማቅረባቸው ማዕቀፉ በሰፊ ሙያዊ ምክክርና በተጨባጭ ልምድ ላይ እንዲመሠረት ያግዛል ተብሏል።
የባለሥልጣኑ የተቋማት ቁጥጥር ኢንስፔክሽንና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሺሻይ አማረ በመድረኩ መጠናቀቂያ ላይ ከምሁራንና ከባለሙያዎች ጋር የተካሄደውን ውይይት አድንቀው፣ በውይይቱ የተገኙ ግብዓቶች ወደ ቀጣይ የማዕቀፍ ዝግጅት ሥራ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።
በቀጣይም በምክክሩ የተሰበሰቡ ሃሳቦችንና ምክረ ሃሳቦችን በማደራጀት፣ በማጠናቀርና በመተንተን ለሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ዝግጅት እንደሚውሉ ተገልጿል። ይህም በሀገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ፣ የጥራት ማረጋገጫ አሠራሩን ይበልጥ ወጥ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂና ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
የሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፉ ዝግጅት የትምህርትና ስልጠና ጥራትን በተቀናጀ መልኩ ለማሻሻል፣ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን የጥራት ባህል ለማጠናከር እና ተማሪዎችና ሰልጣኞች በጥራት የተማሩና በብቃት የተሰለጠኑ የሰው ኃይል እንዲሆኑ ለማስቻል ጠቃሚ እርምጃ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በመሆኑም በአዳማ የተካሄደው የምሁራን ምክክር ሀገራዊ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ዝግጅቱን ከሙያዊ እውቀት፣ ከተጨባጭ ልምድና ከባለድርሻ አካላት ምክረ ሃሳብ ጋር በማጣመር ለመተግበር የሚያስችል ጠንካራ መነሻ መፍጠሩ ተገልጿል።
የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን
በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA
በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA
በዌብሳይት www. neta.gov.et ይከታተሉ።