ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፈቃድ አሰጣጥ የውጭ ገምጋሚዎችን ለማፍራት የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ

ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፈቃድ አሰጣጥ የውጭ ገምጋሚዎችን ለማፍራት የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ ===== = ===== ===== ===== ===== ===== ===== ===== ===== የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ከሰኔ 06-07/2018 ዓ.ም በመልካ አዳማ ሆቴል ስልጠና ሰጠ። ስልጠናው ለውጭ ገምጋሚ እና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፈቃድ አሰጣጥ፣ የክትትል እና ቁጥጥር፣ የጥራት ኦዲት መመሪያዎች እና መስፈርቶች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ እንዲሁም በቀጣይ ሰልጣኝ ባለሙያዎቹ ከባለሥልጣኑ ጋር በጋራ ለመስራት እንዲያስችል ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና አጠቃላይ ትምህርት መሪ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መቅደስ ደረሰ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል። የስልጣናውን አላማ ለማሳካት የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያና መስፈርቶች (በአቶ ብርሃነመስቀል መላክ የቴ/ሙ/ስ ፈቃድ ዴስክ ኃላፊ)፣ የጥራት ኦዲት መመሪያ፣ የጥራት ኦዲት ስታንዳርድና አመልካች፣ የጥራት ኦዲት ሂደት ማኑዋል (በአቶ ኡርጂ ሙሉጌታ የኦዲት ከፍተኛ ባለሙያ)፤ የክትትል እና ቁጥጥር ግምገማ መስፈርቶችና ስታንዳርዶች (በዶ/ር ታምራት ሀይሌ-የቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ)፤ እንዲሁም የገምጋሚዎች ሙያዊ ሥነ-ምግባር እና የፈቃድ አሰጣጥ ሂደት (በአቶ ስማቸው አስሬ-የቴሙስ ፈቃድ ባለሙያ) ባጠቃላይ 4 ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። የቀረቡትን ጽሁፎች መሰረት በማድረግ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በመሪ ስራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ መቅደስ ደረሰ እና በጽሁፍ አቅራቢዎች፤ እንዲሁም ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር በመጡ ተሳታፊ በቂ ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን ለቀጣይ ስራ በእቅድ የሚካተቱ እና ተኩረት የሚሹ በርካታ ግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶችም ከተሳታፊዎች መገኘታቸው ተገልጿል። ባለሥልጣኑ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የታደለ ተቋም መሆኑን ያደነቁት የስልጠናው ተሳታፊዎች በቀጣይም ስታንዳርዶችን የማስተዋወቅ እና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉ ወጥነት እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንደሚመጣ ስልጠናው ያሳደረባቸውን እምነት ተሳታፊዎች ገልጸዋል። በመጨረሻም “ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የተወጣጡ ሰልጣኞች በቀጣይ ባለሥልጣኑ በሚያከናውናቸው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፈቃድ አሰጣጥ ስራዎች ጋር በተያያዘ አምባሳደር ሆናችሁ የምትቀርቡት እናንተው ሰልጣኞች ናችሁ” ያሉት ወ/ሮ መቅደስ ደረሰ ለወደፊት ከባለስልጣኑ ጋር የትብብር ስራዎችን ለማከናወን ማንኛውንም ሙያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ሰልጣኞች ያገኙትን ግንዛቤ ወደ መጡበት ተቋማቸውም የማስረጽ ድርሻቸውን እንዲወጡ መሪ ስራ አስፈጻሚዋ መልዕክታቸውን አስተላለረፈዋል። ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ፤አዳማ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ::