“የጥራት ኦዲት በኢትዮጵያ ተአማኒ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለው የትምህርት እና ስልጠና ስርዓትን ለማረጋገጥ፣ በቀጣይነት ለማሻሻል እና ለሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅዖ ለማድረግ የሚያስችል የባለሥልጣኑ ቁልፍ ተግባር ነው።” የባለሥልጣኑ የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ

“የጥራት ኦዲት በኢትዮጵያ ተአማኒ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለው የትምህርት እና ስልጠና ስርዓትን ለማረጋገጥ፣ በቀጣይነት ለማሻሻል እና ለሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅዖ ለማድረግ የሚያስችል የባለሥልጣኑ ቁልፍ ተግባር ነው።” የባለሥልጣኑ የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ ---------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------- በኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጣና ባለሥልጣን የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ በአካዳሚክ የጥራት ኦዲት የህግ ማዕቀፍ እና የአሰራር ስርዓት ሰነዶች ዙሪያ ከመንግስትና ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ለተውጣጡ የውጭ አካዳሚክ የጥራት ኦዲተሮች ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ስልጠና ተሰጠ፡፡ የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለሥልጣኑ የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ እንዳሉት የጥራት ኦዲት በኢትዮጵያ ተአማኒ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለው የትምህርት እና ስልጠና ስርዓትን ለማረጋገጥ፣ በቀጣይነት ለማሻሻል እና ለሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅዖ ለማድረግ የሚስችል የባለሥልጣኑ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) ወደ ኢፌዲሪ ትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን (ETA) ሲሸጋገር መዋቀሩን ተከትሎ የጥራት ኦዲት የአሰራር ስርዓት ማሻሻያ መደረጉን እና እነዚህ ማሻሻያዎች አዲስ የጥራት ፅንሰ-ሀሳብ እና ስርዓት-ተኮር (System-oriented) የጥራት ኦዲት ሞዴል ላይ የተመሠረተ የጥራት ኦዲት አሰራርን ማስተዋወቃቸውን እና የተሻሻለው የጥራት ኦዲት ማዕቀፍ የተቋማትን የውስጥ ጥራት ማረጋገጫ ስርዓት ውጤታማነትን ለመገምገም ሀገራዊ ግብን፣ የባለድርሻ አካላት ፍላጎት እና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማጣጣም የተቀረፁ የጥራት ኦዲት ስታንዳርዶችን ማካተቱን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ በመላ አገሪቱ በመንግስት እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊና የኘሮግራም የጥራት ኦዲት ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም የኦዲት ግኝት ምክሮችን በመተግበር ላይ ብዙ ክፍተቶች እንደነበሩ የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ በከፍተኛ ትምህርት ጥራት አጠባበቅ ስርዓት ላይ በተለይም ተቋማት ራሳቸውን መገምገም (Self Evaluation) መለማመዳቸው እና የጥራት ፅንሰ-ሀሳቦች ግንዛቤ መፈጠሩ የቀደመው የጥራት ኦዲት ስርዓት ውጤቶች መሆናቸውን አበክረው ገልፀዋል። መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ በቀደመው አስራር ስርዓት ከ3ዐዐ በላይ ኦዲተሮች ሰልጥነው ኦዲት ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ ቢሆንም አዲሱ የጥራት ኦዲት የሕግና የአሠራር ስርዓት ከቀድሞው መሠረታዊ ልዩነቶች ያሉት በመሆኑ የጥራት ኦዲተሮች በአዲስ መልኩ እየሰለጠኑ መሆኑን እና በመጀመሪያ ዙር የኦዲተሮች ስልጠና ከ 50 በላይ ኦዲተሮች ሰልጥነው በፓይለት ኦዲት ስራ ላይ የተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም የጥራት ኦዲተሮች በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት ውስጥ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልፀው ኦዲተሮች በኦዲቱ ሂደት መጠነ ሰፊ የሆነ የጥናትና ምርምር ስራ ላይ የሚሳተፉ በመሆኑ ሥራቸው ስታንዳርድ መጠበቁን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ውስብስብ አካዳሚያዊ፣ አስተዳደራዊ እና ተቋማዊ ስርዓቶችን በከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነት በመገምገምና ውሳኔ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሪት ምስራቅ አሰፋ በበኩላቸው የስልጠናው ዋና ዓላማ የጥራት ኦዲት የሕግ ማዕቀፍ እና የአሰራር ሰነዶች ለውጪ የአካዳሚክ ጥራት ኦዲተሮች ማስተዋወቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በስልጠናው ላይ በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፣ የዴስክ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የተለያየ ይዘት ያላቸው ገለፃዎችን አቅርበዋል፡፡ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣንን ታሪካዊ ዳራና አሁናዊ ለውጦች እና የጥራት ኦዲት ሞዲል(ADRI) በጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ በወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ፤ የከፍተኛና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና መመሪያ በከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት የዴስክ ኃላፊ በሆኑት በአቶ አብይ ገዛኽኝ ፤ የጥራት ማጎልበቻ እቅድ እና የክትትል ኦዲት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና የጥራት ኦዲት የዴስክ ኃላፊ በሆኑት በአቶ እሸቱ እዬብ፤የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ስታንዳርዶች እና ውጤት አመላካቾች የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት ባለሙያ በሆኑት በወ/ሮ ውብነሽ ሽፈራው፤ የጥራት ኦዲት ፕሮሲጀር እና የግለ ግምገማ አዘገጃጀት የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት ባለሙያ በሆኑት በአቶ ነዋይ ሙሉ፤ የጥራት ኦዲት ሪፖርት አጻጻፍ የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት ባለሙያ በሆኑት በአቶ ሁርጂ ሙሉጌታ እና የጥራት ኦዲተሮች ምልመላና መረጣ የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት ባለሙያ በሆኑት በአቶ ዳኝነት አምሳሉ የጥራት ኦዲተሮች ምልመላና መረጣ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በስልጠናው ላይ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደረጃ እንግዳ የአካዳሚክ የጥራት ኦዲት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል እንዲሁም የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እየተገበረ ስላለው አዲስ የጥራት ኦዲት ስርዓት ማብራራያ ሰጥተዋል፡፡ አክለውም ስለ ጥራት ማረጋገጫ ዘዴዎች፤ የጥራት ኦዲት አስፈላጊነት፤ስለተቋማዊ ጥራት ኦዲት፤ADRI የጥራት ሞዲል ከተለመደው(Traditional model) የጥራት ኦዲት ሞዴሎች ጋር ስላለው ልዩነት፤የADRI የጥራት ኦዲት ሞዴልን መጠቀም ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንዲሁም በጥራት ኦዲት ሥራ ላይ ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡ የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስልጠናው በጥራት ኦዲት ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ያሳደገላቸው መሆኑን እና በተለይም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ደረጄ እንግዳ ያካፈሉት ልምድ ትልቅ መነሳሳት የፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀው ኘሬዚዳንቱ ተመሳሳይ ስልጠና በበይነ መረብ በየደረጀው ላሉ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች መስጠት ያለባቸው መሆኑንና የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣንም ይህንን ማመቻቸት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋላ ስልጠናውን መሠረት ያደረግ ምዘናም ወስደዋል፡፡ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ የጥራት ኦዲት ሥራ የተቋማት አመራሮችን ቁርጠኝነት የሚጠየቅ መሆኑን ገልጸው ይህንን ኃላፊነት ለማስገንዘብ ባለሥልጣኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን የሚያዘጋጅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የኦዲተሮች አቅም የመገንባት ሥራም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።