የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደራዊ መዋቅር እና የእውቅና አሰጣጥ ስታንዳርዶች ከአህጉራዊ የጥራት ማረጋገጫ ጋር ያላቸውን መጣጣም አስመልክቶ የፖሊሲ የውይይት መድረክ ተካሄደ
የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደራዊ መዋቅር እና የእውቅና አሰጣጥ ስታንዳርዶች ከአህጉራዊ የጥራት ማረጋገጫ ጋር ያላቸውን መጣጣም አስመልክቶ የፖሊሲ የውይይት መድረክ ተካሄደ ------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------ የኢፊዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደራዊ መዋቅር እና የእውቅና አሰጣጥ ስታንዳርዶች ከአህጉራዊ የጥራት ማረጋገጫ ጋር ያላቸውን መጣጣም አስመልክቶ ጥር 20 ቀን 2018 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄደው የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ የጀርመን አካዳሚክ ኤክስቼንጅ ሰርቪስ (DAAD) ተወካይ እና የትብብር፣ የፓርትነርሽፕ ፕሮግራሞች፣ የቀድሞ ተማሪዎች ፕሮጀክቶችና የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር ከፍተኛ የዴስክ ኦፊሰር ወ/ሮ ሳራ ላንግ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የኘሮጀክቱ ዓላማ የፓን አፍሪካን የጥራት አጠባበቅ ማእቀፍ ለከፍተኛ ትምህርት ጥራት አጠባበቅ ያለውን ፋይዳ ማስተዋወቅና የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተስማሙበትን የጋራ ስታንዳርድ እንዲቀጠሙ ማበረታታት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ሳራ የአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድ(ASG-QA)፣የጥራት ማረጋገጫ ጋይድላይን እና የከፍተኛ ትምህርት ወሳኝ ሚና አላቸው፤ ሰነዱ ከተዘጋጀ አስር ዓመት የሞላው ቢሆንም ከአፍሪካ ከሁሉም ቀጠናዎች በመጡ አፍሪካዊ ባለሙያዎች እና በአፍሪካ ህብረት ቀጠና እና ሀገራት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድ(ASG-QA) እና ጋይድ ላይኖች ስብስብ ለውስጥና ለውጭ የጥራት ማረጋገጫ ቅድመ ሁኔታ ሳይሆኑ ውጤትን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና በሀገራዊ የጥራት ባለሥልጣኖች ውስጥ ጥራትን የማረጋገጫ ዘዴዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የጋራ ስታንዳርዶችና መመዘኛዎች የተቀመጡ ቢሆንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በግላቸው እና የሀገር አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ኤጀንሲዎች በራሳቸው አውድ እና ተቋማዊ ባህል የሚያንጸባርቅ ስታንዳርድ መጨመር የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በባለሥልጣኑ የስታንዳርዳይዜሽንና የብቃት ማረጋገጫ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ሀብታሙ ተሾመ በበኩላቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የውይይት መድረኩ ሀገራችን በአዲስ መልኩ ትኩረት በመስጠት እያደረገች ላለችው ሁሉን አቀፍ የትምህርትና ስልጠና ማሻሻያ በተለይም ለከፍተኛ ትምህርት ስርዓታችን ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ፡፡ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የትምህርት እና ስልጠናዎች ጥራትን ለማስጠበቅ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልእኮ ከአፍሪካ ስታንዳርዶች እና የጥራት ማረጋገጫ ጋይድ ላይኖች ጋር በማቀናጀት በመላው አፍሪካ የታመነ፣ ግልጽ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓትን ለመፍጠር እና የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደራዊ መዋቅር እና የእውቅና አሰጣጥ ስታንዳርዶች ከአህጉራዊ የጥራት ማረጋገጫ ጋር ለማጣጣም በተቀናጀ የአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና እውቅና ኢኒሼቲቭ (HAQAA3) ተነሳሽነት የተዘጋጀው የፖሊሲ የውይይት መድረክ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የጥራት ኦዲት መሪ ስራ አስፈፃሚ እና የተቀናጀ የአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና እውቅና ኢኒሼቲቭ (HAQAA3) አምባሳደር ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ የዚህ የፖሊሲ ውይይት ዓላማ ብሄራዊ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ የአፍሪካ የጥራት ማረጋገጫ ማዕቀፎችን (ASG-QA) የጋራ ግንዛቤን ለማጠናከር በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር መዋቅሮች፣ የእውቅና አሰጣጥ እና አህጉራዊ የጥራት ማረጋገጫ ተስፋዎችን የሚያሻሽሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መለየት መሆኑን ገልጸው በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲን እና የቁጥጥር ማሻሻያዎችን ለመደገፍ የተጠናከረ የባለድርሻ አካላት ስምምነት እና ኢትዮጵያ በHAQAA3 እና በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ በአህጉራዊ የጥራት ማረጋገጫ ውጥኖች ላይ ለምታደርገው ቀጣይ ተሳትፎ የላቀ ሀገራዊ ዝግጁነት ከሚጠበቁ ውጤቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥራት ኦዲት ዳይሬክተር እና የፕሮጀክቱ ቡድን አባል አቶ አብነት ተሾመ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የአፍሪካ ስታንዳርዶች እና የጥራት ማረጋገጫ ጋይድ ላይኖች ከትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የእውቅና ስታንዳርዶች ጋር በማነጻጸር የጥናት ውጤቶች እና ምከረ ሀሳቦችን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኤባ ሚጀና ቀጣይ ጊዜ የአጭር እና የረጅም ጊዜ በትምህርት ሚኒስቴር ሊከናወኑ የታቀዱትን ተግባራት ሁሉም ፖሊሲዎቻችን ከዓለም አቀፍ እና ከአህጉራዊ ደረጃዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ የፖሊሲ ማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ፕሮግራሞች ሲከፈቱ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ያለበቂ ጥናት ሳይሆን በቂ ጥናት ተደርጎበት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት እና የማጠቃለያ ላይ የመዝጊያ መልእክት ያስተላለፉት የባለሥልጣኑ የእውቅና እና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ስታንዳርዶች የተለያዩ እና የተለያየ ዓላማዎች ያሉት መሆኑን ገልጸው ነገር ግን አንዳንድ ስታንዳርዶች መመሳሰል ስላለባቸው የኦዲት እና የእውቅና ስታንዳርዶችን በግምገማ ላይ ነን። እውቅና ለመስጠት ተቋማት ኦዲት መደረግ አለባቸው፡፡ የእውቅና እና የኦዲት ስራ እርስ በእርሱ የሚመጋገብ ነው፡፡ ከዚህ የውይይት መድረክ ያገኘናቸው ግብአቶችን በመጠቀም ሁላችንም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ የተቀናጀ የአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና እውቅና ኢኒሼቲቭ (HAQAA3) እና ውይይቱን በትብብር ያዘጋጁትን አካላት አመስግነዋል፡፡ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ከፍተኛ አመራሮች፣የትምህርት ሚኒስቴር፣ ፣የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች እና በበይነ መረብ የሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ምክትል አካዳሚክ ፕሬዝደንቶችና የጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክተሮች በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።
