22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ
ህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች 22ኛውን የዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ። የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን“ትውልድን በሥነምግባር-ተቋማትን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው። በመድረኩ የመክፈቻ ንግግሩ ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብረሃኑ ነጋ እንደ ሀገር ከገጠመን የሥነ ምግባርና የሞራል ክስረት ለመላቀቅ ትውልዱ ሁለንተናዊ ብቃትና ስብዕና የተላበሰ ሆኖ እንዲቀረጽ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የሙስና ተግባር ን ለመከላከል የመንግሥት አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች በእኩልነት መስጠት፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም እና የአሠራር ግልጽነትን ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ሙስና ፈጽመው በተገኙ ዜጎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች አስተማሪ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ በፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው የኑሮ ውድነት፣ብልሹ አሰራር፣መንደርተኝነትና ጠባቂነት ሙስናን ለመከላከልና ለመቀነስ የሚደረገውን ትግል እየተፈታተኑት ቢሆንም ከሁሉም ሴክተር መ/ቤቶች፣ ከሀይማኖት ተቋማት እና ከመላው ህብረተሰብ ጋር በቅንጅት በመስራት የሚለገውን ውጤት ማምጣት የሚቻል መሆኑን ገልጸው የተረጋጋችና ያደገች ሀገር እንድትኖረን ህጻናትን በሥነ-ምግባር ገንብቶ ማሳደግና ሙስናን መታገል ዜጎች በቁርጠኝነት የሚሰሩት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል። በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ሙስና ሀገራችንን ወደ ቁልቁለት እየወሰደ ያለ ዋነኛው የእድገት ጸር በመሆኑ መንግሥት ከመከላከል ጎን ለጎን ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው የትምህርት ዘርፍ ሙስናን የሚጸየፉ ዜጎችን ለማፍራት እና ሙስናን የመታገል ተቋማዊ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ሁሉም የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ትግሉን ከራስ በመጀመር አጠናክረው ሊቀጥሉበት እንደሚገባ አሳስበዋል። በዝግጅቱ ላይ በፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተዘጋጀ በተቋማት አሰራርና ሙስና መከላከል ላይ ያተኮረ የድምፅ መልእክት ሰነድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ በመጨረሻም የትምህርት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ ከፍተኛ አመራሮች የሀብት ምዝገባ ሰነድን ለፌዴራል የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስረክበዋል። የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ ።
