‘የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ልህቀት እና የማሰብ ችሎታ ለትምህርት ጥራት ያለው አስተዋጽዖ’ በሚል ርዕስ ሴሚናር ተካሄደ

የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ልህቀት እና የማሰብ ችሎታ ለትምህርት ጥረት ያለው አስተዋፆኦ በሚል ርእስ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ሲሚናር ላይ የመክፈቻ ንግግረ ያደረጉት በባለሥልጣኑ የእውቅና እና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሣ የትምህርት ስርዓት ፍትሃዊነት በሀገራችን ትልቁ ችግር ነው። በገጠርና በከተማ እና በከተማ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ የትምህርት ጥራት ትልቅ አጀንዳ ነው፤ ነገር ግን ከግንዛቤው አንስቶ እስከ ትግበራው በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ አይደለም። በዚህ ውስጥ የእኛን ግዴታ እና ኃላፊነት ለመወጣት ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። ያገኘነውን እድል ሁሉ ተጠቅመን እራሳችንንም በየጊዜው ማብቃት አለብን። እንዲህ አይነት ሴሚናር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ተቀራርቦ ለመወያየት፤ በስራ ሂደት የገጠሙንን ችግሮች እዚህ አምጥተን ለመማማር እንዲሁም በርካታ የጥናት እና ምርምር ሀሳቦችን ለማግኘት የሚጠቅም መድረክ በመሆኑ በተቋም ውስጥ መለመድ አለበት። ስለዚህ ሁሉም ሠራተኛም ሊሳተፍ ይገባል፤ አዘጋጁ የስታንዳርዳይዜሽንና የብቃት ማረጋገጫ ሥራ አስፈጻሚው እና የመወያያ ሀሳብ አቅራቢዎች ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል። በሲሚናሩ ላይ የመወያያ ሀሳብ ያቀረቡት በባለሥልጣኑ የስታንዳርዳይዜሽንና የብቃት ማረጋገጫ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሀብታሙ ተሾመ በበኩላቸው የተሻሻለው የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ልዕቀት እና የማሰብ ችሎታ ለትምህርት ጥራት ያለው አስተዋጽዖ ሀሳቡ እጅግ ሰፊ ቢሆንም በተቋማችን በሚሰሩ የትምህርት ጥራትንን የማረጋገጥ ሥራዎች ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራዎቻቸውን ችግር ፈቺ ፣ የፈጠራ አቅምን የሚያሳድግ እና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል የማስተማር ስነ-ዘዴ እንዲከተሉ ለማድረግ መሠረት የሚሆኑ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመረዳት የሚያስል መሆኑን ገልጸዋል። የትምህርት ተቋማትም ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ፣ ተማሪ ተኮር፣ የሰው ልጅ ውስብስ ተፈጥሮ እንዳለው በመረዳት የተማሪዎቻቸውን ተሰጥዖ፣ ባህሪ እና ያሉበትን ሁኔታ በመረዳት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ውይይቱን የመሩት በባለስልጣኑ የእውቅና መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተረፈ በላይ በመማር ማስተማር ስራ ውስጥ የሚገኙት ሁሉም መሰረታዊ ጉዳዮች ሊሟሉ እንደሚገባ እና የባለስልጣኑ ሠራተኞችም እይታቸው ሁሉንም ያማከለ መሆን አለበት ብለዋል። ከተሳታፊዎች በርካታ ሀሳቦች እና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተድርጎባቸዋል። በመጨረሻም የባለሥልጣኑ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተምሩ መስፍን ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር በባለሥልጣኑ ሲሚናሩ መጀመሩ መልካም እና የነበረው የተሳትፎ ሂደት ጥሩ እንደነበረ ገልጸው ከዚህ ቀደም የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ሂደት ከዚህ ቀደም የተሰሩ እና ወደፊት በሚሰሩ ስራዎች ላይ መሠረት ያደረጉ ርእሶችና ሀሳቦች ለጽ/ቤቱ ቀርበው እንዲመረጡ እና ሴሚናር የማዘጋጀቱ ስራ መደበኛ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው አዘጋጁ የሥራ ክፍል እና የመወያያ ሀሳብ አቅራቢውን ላደረጉት ጅማሮ እና ተነሳሽነት አመስግነዋል። የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።