በከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፈቃድ እና ፈቃድ እድሳት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 988/2016 መሠረት የፈቃድ ዕድሳት መስፈርቶች፡-
**የፈቃድ እድሳት ያቀረበ ማንኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ወይም ፕሮግራም በባለስልጣኑ የተቀመጡትን የፈቃድ እድሳት መስፈርቶች አሟልቶ ሲገኝ ለአምስት (5) ዓመት ፈቃዱ ይታደስለታል፤ ** የፈቃድ እድሳት ጥያቄ ያቀረበ ማንኛውም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋም፣ የአጫጭር ስልጠና፣ የሙያ ምዘና፣ የፕሮግራም እውቅና እና የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በባለስልጣኑ የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው ሲገኙ ባለስልጣኑ ለሶስት (3) ዓመት ፈቃዱን ያድስላቸዋል፤ ** በሰነድ ምርመራ ወቅት ሰነድ ያጓደለ ተቋም በአርባ አምስት (45) ቀናት ውስጥ አሟልቶ ማቅረብ ይኖርበታል። የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ካለፈ ተቋሙ በገዛ ፈቃዱ የፈቃድ እድሳት ሂደቱን እንዳቋረጠ ተቆጥሮ በዘጠና (90) ቀናት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን መመዘኛዎች በማሟላት በድጋሚ ሊያመለክት ይችላል። ** የፈቃድ እድሳት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከለከለ ማንኛውም ተቋም ወይም ፕሮግራም በባለሥልጣኑ የተገለፁትን የተጓደሉ መመዘኛዎች አሟልቶ በዘጠና (90) ቀናት ዉስጥ እንደገና ሊያመለክት ይችላል። የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ካለፈ ተቋሙ በገዛ ፈቃዱ የፈቃድ እድሳት ሂደቱ እንዳቋረጠ ተቆጥሮ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ በተቀመጠው መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል፤ ** በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት አመልክቶ የፈቃድ እድሳት የተከለከለ ተቋም የተቀበላቸውን ተማሪዎች በትምህርት መስኩ ፈቃድ ወዳለው ሌላ ተቋም ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወይም እንዲማሩ በማድረግ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ለባለስልጣኑ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ** የፈቃድ እድሳት የተከለከለ ወይም ተማሪ አዛውር የተባለ ተቋም ዉሳኔው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በተከለከለበት የትምህርት መስክ ከሁለት ዓመት በኋላ በድጋሚ እንደ አዲስ ሊያመለክት ይችላል እና ** ተቋማት ላቀረቡት የፈቃድ እድሳት ጥያቄ ባለስልጣኑ በአካል ተገኝቶ መገምገም የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ወቅቱ በፈቀደው ቴክኖሎጂ አማካኝነት ወይም በሌሎች አማራጮች መስፈርቱን በማያጓድል ሁኔታ ሊገመገም እና ጊዜያዊ የፈቃድ ሰርተፊኬት ሊሰጥ ይችላል። ፈቃድ ወይም ፈቃድ እድሳት መሰረዝ ** ፈቃድ አግኝቶ ሲሰራ የቆየ ማንኛውም ተቋም የፈቃድ እድሳት በወቅቱ ካልጠየቀ ባለስልጣኑ ፈቃዱን ሊሰርዝ ይችላል፤ ** ማንኛውም ተቋም ወይም ፕሮግራም በባለስልጣኑ የተቀመጡ መስፈርቶችን አጓድሎ ሲገኝ እና በግምገማ ሲረጋገጥ የተሰጠው ፈቃድ ወይም ፈቃድ እድሳት ይሰረዛል፤ ** ማንኛዉም በድንበር ተሻጋሪ ትምህርት መርሃ-ግብር የሚያስተምር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በዉጭ ሀገር ያለዉ ተቋም እዉቅናዉ ካልታደሰ በሀገር ዉስጥ ያለዉ ተቋም የመርሃ ግብሩ እና የትምህርት መስኩ ፈቃዱ ይሰረዛል እና ** ማንኛውም ተቋም ወይም ፕሮግራም የትምህርት ጥራትን ካጓደለ፣ የከፍተኛ ትምህርት አሰጣጥ ህጎችን ከጣሰ እና የእግድ ቅጣት ተላልፎበት ካላሻሻለ በባለስልጣኑ የተሰጠው ፈቃድ ይሰረዛል ናቸው። የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።
