የቀድሞ እና አዲሱ የጥራት ኦዲት አሰራር ውጤቶች እና ተግዳሮቶቹ
#1. #የቀድሞ_የጥራት_ኦዲት_አሰራር_ውጤቱና_ተግዳሮቶቹ_ውጤቱ የከፍተኛ ትምህርትና አግባብነት ጥራት ኤጀንሲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሬ ለሁለት አስርት ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር የጥራት ኦዲት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የትምህርት ጥራት ከማስጠበቅና ከምሩቃን ውጤታማነት ረገድ ምን ተፅኖ አመጣ የሚለው በጥናት መረጋገጥ ያለበት ሆኖ በተቋማት ላይ የሚከተሉትን ለውጦች አምጥቷል፡- ለተቋማት በኤጀንሲው ይሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ስለ ጥራት አጠባበቅና የጥራት ፅንሰ ሀሳብ አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር መደረጉ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኘሮግራሞቻቸው ላይ ጥራት ለማስጠበቅ እየተካሄደ ላለው የጥራት ኦዲት ሪፎርም ሥራ መሠረት ጥሏል፡፡ የጥራት ኦዲት በማከናወን ሂደት አንዱ መስፈርት ተቋማት በተቀመጡ የትኩረት መስኮች መሠረት ግለ ግምገማ ማካሄድ ነው፡፡ ይህ ልምምድ ባለሥልጣኑ አሁን ለጀመርነው የጥራት ኦዲት ሥራ አቅም ለመፍጠር ችሏል፡፡ #ተግዳሮቶች፦ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 351/1995 የተቋቋመው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራትን እና አግባብነትን የማረጋገጥ ሥልጣን ተሰጠው። ይሄንን መሠረት በማድረግ በበርካታ ተቋማት ላይ የጥራት ኦዲት ሲያከናውን እና በኦዲት ግኝቶቹ መሠረት ምክረ ሃሳቦችን ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም ኤጀንሲው ያስቀመጠውን የጥራት ኦዲት ዓላማ ማሳካት አልቻለም ነበር፡፡ ዓላማውን እንዳያሳካ ካደረጉ ተግዳሮቶች መካከል የሚከተሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፦ #ተጠያቂነትን_የሚያረጋግጥ_አሰራር_አለመኖር፦ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የጥራት ኦዲት ግምገማዎችን ሲያከናውን እና በኦዲት ግኝቶቹ መሠረት ምክረ ሀሳቦችን ለተቋማት ሲሰጥ ቢቆይም ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የማስፈጸሚያ መመሪያና ስታንዳርድ እንዲሁም ዘዴዎች ባለመኖራቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥራት ኦዲት ግኝት መሠረት የተሰጡ ምክረ-ሀሳቦችን ተጠቅመው የአሠራር ስርዓታቸውን ባያሻሽሉ ኤጀንሲው ምንም ዓይነት እርምጃ እየተወሰደ አልነበረም፡፡ #ኤጀንሲው_የሚከተለው_የጥራት_ፅንሰ_ሃሳብ_ውስንነት_የነበረበት_መሆኑ ፡- የቀደመው የጥራት ኦዲት ማዕቀፍ የጥራት ፅንሰ-ሃሳብ (የጥራት ትርጓሜ) "fitness for purpose" ማለትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምን ያህል ተቋማዊ ዓላማቸውን እንዳሳኩ በመገምገም ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። ይህም ሌላኛውን የጥራት ፅንሰ-ሃሳብ ("fitness of purpose") ማለትም የተቋማቱ ግብ ከባለድርሻ አካላት ፍላጎቶች ጋር የተጣጣሙ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ላይ የሚያተኩረውን ፅንሰ-ሃሳብን የዘነጋ እና ጥራትን በአንድ ፈርጅ ብቻ የሚመለከት ማዕቀፍ ነበር። #የስርዓት_ተኮር_የጥራት_ኦዲት_ማእቀፍ_አለመኖር፡- የጥራት ኦዲት መስፈርቶች በተቋማዊ ስትራቴጂካዊ ግብ፣ ትግበራ፣ ውጤት እና ተከታታይ መሻሻል መካከል ያለውን ትስስር ለመገምገም በሚያሰችል መልኩ የተዋቀሩ አልነበሩም።ይህም ትርጉም ያለው እና ዘላቂ የሆነ የጥራት ማሻሻልን ለማረጋገጥ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። #በግብአት_ሂደት_ውጤት_ላይ_ብቻ_ያተኮረ_መሆኑ፡- የቀደመው የጥራት ኦዲት ማዕቀፍ በግብአት-ሂደት-ውጤት (IPO) ሞዴል ላይ የተመሠረተ እና ለእያንዳንዱ የጥራት ኦዲት መስፈርት የተቋማትን ግብና የአተገባበር ስልትን፣ ትግበራን፣ ውጤትን ከግብና አተገባበር ስልት አንፃር ለመለካት እና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ መሻሻል መደረጉን ለመገምገም እንዲሁም በዕቅድ፣ ስልት፣ ውጤት፣ እና መሻሻል መካከል ያለውን ትስስር እና ቅንጅት ለመገምገም የሚያስችሉ የጥራት አመላካቾች አልነበረውም። #የጥራት_ኦዲቱ_በመደበኛ_መርሃ_ግብር_የሚሰጡ_የትምህርት_መስኮች_ላይ_ብቻ_ያተኮረ_መሆኑ፡- የቀደመው የጥራት ኦዲት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መደበኛ ኘሮግራሞቻቸው ላይ ብቻ ያተኮረ፤ በድህረ ምረቃ፣ በርቀት፣ በበይነ መረብ፣ በክረምት መረሃ ግብር የሚሰጡትን የከፍተኛ ትምህርት መስኮች የማያካትት ነበር፡፡ #2. #አዲሱ_የጥራት_ኦዲት_አሰራር ኤጀንሲው በተቋቋመበት አዋጅ ላይ ጥራት ማስጠበቅን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በግልፅ ተለይተው አልተቀመጡም ነበር፡፡ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ላይ ማሻሻያ የተደረገ ቢሆንም በጥራት ኦዲት ግኝቱ መሠረት የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ያለማድረግ ልምምድ የቀጠለበት ሁኔታ ነበረ፡፡በመጀመሪያው የጥራት ኦዲት ዑደት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች በሁለተኛው ዙር የኦዲት ዑደት መደገማቸው አንድ ማሳያ ነው፡፡ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የጥራት ኦዲት ማዕቀፍን አሻሽሏል። ይህ ማሻሻያ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ላይ ያተኮረ የውስጥ ጥራት ማረጋገጥ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል ነው። አዲሱ የጥራት ኦዲት ማዕቀፍ እና ያካተታቸው ዋና ዋና ማሻሻያዎች የሚከተሉት ናቸው:- #ተቋማዊ_ተጠያቂነትን_የሚያረጋግጥ_የተጠናከረ_የህግ_ማዕቀፍ፦ ባለሥልጣኑ በቀድሞው የጥራት ኦዲት አሰራር ስርዓት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2011 የተቀመጡ ነገር ግን ተግባራዊ ያልተደረጉ የሕግ ድንጋጌዎችን እንዲሁም የባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 515/2014 ላይ የተቀመጡ የጥራት ኦዲት ሕጎችን መሠረት በማድረግ የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መመሪያና ስታንዳርዶችን አዘጋጅቷል።ይህ ሕግ ተቋማዊ የጥራት ኦዲት ምክረ ሀሳቦችን አለመተግበር ተቋማዊ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል የሚያረጋግጥ ነው፡፡ #የተሻሻለ_የጥራት_ፅንሰ_ሀሳብ_ብያኔ፦ "fitness for purpose" ላይ ብቻ ያተኮረ የነበረውን የጥራት ፅንሰ-ሃሳብ ብያኔ "Fitness of purpose" የጥራት ፅንሰ-ሃሳብ ብያኔንም ጭምር እንዲያካትት ተደርጓል። የጥራት ኦዲት ጥራትን እንደ "fitness for purpose" ሲበይን የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያስቀመጡትን ተልዕኮ፣ ራእይ እና ስልታዊ ዓላማዎችን በብቃት እያሳኩ መሆናቸው ይገመግማል። የጥራት ኦዲት ጥራትን እንደ "fitness of purpose" ሲበይን የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተልዕኮ፣ ራእይ እና ስልታዊ ዓላማዎችን ተገቢነት፣ ተዛማጅነት እና ከባለድርሻ አካላት ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸው ይገመግማል። በመሆኑም ይህ ድርብ የጥራት ብያኔ ተቋማቱ የተቀመጡትን ግቦች ማሳካታቸውን ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች እና ከባለድርሻ አካላት ፍላጎቶች ጋር መጣጣማቸው እንዲገመገም አድርጓል። በተጨማሪ የጥራት ኦዲት ትኩረት ከግብዓት ግምገማ ወደ የተቋማዊ ተልእኮ አፈፃፀም ግምገማ እና የአሰራር ስርዓት ውጤታማነት ግምገማ እንዲሸጋገር አድርጓል። #ADRI_ሞዴል፦ በቀደመው አሰራር ውጤታማ ያልነበረውን ግብአት-ሂደት-ውጤት (IPO) ሞዴልን በመተካት የADRI ሞዴል በተሻሻለው የጥራት ኦዲት ማዕቀፍ እንዲተገበር ተደርጓል። ADRI ሞዴል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውና ዑደታዊ የጥራት ማረጋገጫ ሞዴል ሲሆን የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ግብና ዓላማን ከትግበራ፣ ውጤቶች እና ቀጣይነት ካለው መሻሻል ጋር በማገናኘት ሁሉን አቀፍ፣ ዑደታዊ ግምገማ ለማከናወን የሚረዳ ስልት ነው። ADRI ሞዴል የተቋማት አፈፃፀም በእያንዳንዱ የጥራት ኦዲት መስፈርት ስር በአራት ተያያዥነት ያላቸው ገፅታዎች እቅድና ስልት (Approach)፣ ትግበራ (Deployment)፣ የተመዘገቡ ውጤቶች (Results) እና ማሻሻያዎች (Improvements) አንፃር መገምገም ያስችላል። ይህ ሞዴል የተቀናጀ እና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ አሰራርን የሚተገብር ቀጣይነት ያለው መሻሻልን የሚያጎለብት፣ የጥራት ማረጋገጫው ሙሉ በሙሉ ወደ ተቋማዊ ስትራቴጂካዊ ግቦችና የትግበራ እቅዶች እንዲሁም ሥራዎች ጋር የተዋሃደ መሆኑን የሚያረጋግጥ እና ለግብ አፈጻጸምም፣ ለሂደቱ ውጤታማነት እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ነው። የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።