የጥራት ኦዲት ምንነት፣የጥራት ኦዲት የሚካሄድበት ዓላማ እና ባለስልጣኑ የሚያከናውነው የጥራት ኦዲት ዋና ዋና ዓላማዎች

1. የጥራት ኦዲት ምንድነው? የጥራት ኦዲት” ማለት የትምህርትና ስልጠና ተቋም ወይም ፕሮግራም ውጤታማ የጥራት ማረጋገጫ ስርዓት ዘርግቶ እየተገበረ መሆኑን ለማረጋገጥ በኢፌድሪ ትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን የሚከናወን ተቋማዊ ወይም ፕሮግራም ተኮር ግምገማ ነው። የጥራት ኦዲት በኢትዮጵያ ተአማኒ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነት ያለው የትምህርት እና ስልጠና ስርዓትን ለማረጋገጥ፣ በቀጣይነት ለማሻሻል እና ለአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅዖ ለማድረግ የሚስችል የባለስልጣኑ ቁልፍ ተግባር ነው። ባለስልጣኑ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ (HERQA) ወደ ኢፌድሪ ትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን (ETA) ሲሸጋገር መዋቀሩን ተከትሎ የጥራት ኦዲት የአሰራር ስርዓት ማሻሻያ ተደርጓል። እነዚህ ማሻሻያዎች አዲስ የጥራት ፅንሰ-ሀሳብ እና ስርዓት-ተኮር (System-oriented) የጥራት ኦዲት ሞዴል ላይ የተመሰረተ የጥራት ኦዲት አሰራርን አስተዋውቀዋል። የተሻሻለው የጥራት ኦዲት ማዕቀፍ የተቋማትን የውስጥ ጥራት ማረጋገጫ ስርዓት ውጤታማነትን ለመገምገም ሀገራዊ ግብን፣ የባለድርሻ አካላት ፍላጎት እና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማጣጣም የተቀረፁ የጥራት ኦዲት ስታንዳርዶችን አካቷል። 2. የጥራት ኦዲት የሚካሄድበት ዓላማ? ትምህርትና ስልጠና ድህነትን ለማሸነፍ እና ሀገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ጥራቱን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። የኢፌድሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሀገራዊና የዓለምአቀፍ ደረጃን የጠበቀ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ እና ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ተመራቂዎችን እንዲያፈሩ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ የጥራት ማረጋገጥ ስራዎችን ያከናውናል ከእነዚህ ተግባራት አንዱ እና ዋነኛው በትምህርትና ስልጠና ተቋማት ላይ የሚያከናውነው የጥራት ኦዲት ነው። ባለስልጣኑ የሚያከናውነው የጥራት ኦዲት የሚከተሉት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት:- ------------------------------------------------------------------ ---------------- 1) የጥራት ኦዲት ዋንኛ ዓላማ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ቀጣይነት ያለው የትምህርት ጥራት መሻሻልን ለማረጋገጥ ያለመ ሲሆን የተቋማት ጠንካራ ጎኖችን እና መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት የመማር ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ራዕይና ተልዕኮቻቸውን ማሳካት የሚያስችል ቀጣይነት ያለውና በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ የውስጥ ጥራት አጠባበቅ ስርዓት መተግበራቸውን ማረጋገጥ ነው። 2) የጥራት ኦዲት የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ውጤታማ የሀብት አጠቃቀምን በማረጋገጥ ተልዕኳቸውን መፈፀማቸውን በመገምገም ለባለድርሻ አካላት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ነው። 3) የጥራት ኦዲት በትምህርትና ስልጠና ተቋማት ላይ ባለስልጣኑ ያከናወነውን የጥራት ኦዲት ግኝቶችን እና የተቋማቱን የውስጥ ጥራት አጠባበቅ ስርዓት የውጤታማነት ደረጃን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ባለድርሻ አካላት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉ፣ በትምህርት ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለማስቻል እና ግልፀኝነትን ለማረጋገጥ ነው። 4) የጥራት ኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን በመጠቀም የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ፖሊሲዎቻቸውን፣ ስርዓተ-ትምህርቶቻቸውን እና የውስጥ ጥራት አጠባበቅ ስርዓቶቻቸውን ከሀገራዊ እና ተቋማዊ ተልእኮዎች ጋር አጣጥመው እንዲሰሩ ማድረግ ነው፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።