“የጥራት ኦዲት ስልጠናው በአካዳሚክ ዘርፉም የተሻለ ሆነን እንድንገኝ የሚያስችለን ነው”- ዶ/ር ወንደሰን አምታታው - በየካቲት12 ሆስፒታል ሚዲካል ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ቤት ዲን እና የኢንዶክሪን ሰርጀሪ ሰብእስፒሻሊስት

ከሰኔ 4 እስከ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በየካቲት12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አካዳሚክ ጥራት ኦዲት መመሪያ፤ የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጥራት ኦዲት ስታንዳርድ ፤ ውጤት አመላካቾች እና የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ለሆስፒታሉ ሀኪሞች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ስልጠና ተሰጠ። የኮሌጁ ዲን ዶክተር ወንድወሰን አምታታው በመክፈቻ ንግግራቸው ከበርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የእኛን ተቋም ለፓይለት ኦዲት ስለመረጣችሁ እናመሰግናለን ብለዋል:: የጥራት ጉዳይ ለነገ የማይባል ሲሆን ብቁ የሰዉ ኃይል ለመፍጠርና ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት የሚረዳን ከመሆኑ ባሻገር ይህ ስልጠና የዉስጥ ጥራት ኦዲት ስርዓታችን ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን እንድንሰራ ዕድል የሚፈጥር ነው:: የሆስፒታላችንን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ እና ቀልጣፋ አሰራርን የተከተለ ለማድረግ እንደቻልነው ሁሉ የጥራት ኦዲት ስልጠናው በአካዳሚክ ዘርፉም የተሻለ ሆነን እንድንገኝ የሚያስችለን ነው ብለዋል። የሆስፒታሉ የአስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሮቮስት አቶ ዓለሙ ክብረት በበኩላቸው በህክምናው የጀመርነውን የጥራት ኢንሺቲቭ በትምህርቱም ለመድገም ጥረት ስናደርግ ነበር፡፡የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ተቋማችን ሳይመጣ የተወሰኑ ጥረቶችን ስናደርግ የነበረ ቢሆንም ባለሥልጣኑ ለጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ስታንዳርድ ቅረቡ የሚል ሐሳብ ይዞ መምጣቱ ለእኛ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የጀመርነውን ጥራትን የማረጋገጥ ሥራ ለማጠናከር እና ግዴታችንን ለመወጣት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናል። ስለዚህ ያገኘነውን መልካም አጋጣሚ አንጠፍጥፈን ምንም ሳይቀር እንጠቀማለን። በማንኛውም ጊዜ ከእኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ቃል እንገባለን። የተሰጠንንም አሳይመንት ለመወጣት አስፈላጊውን ክትትል እናደርጋለን። ሰልጠኞችም ያገኙትን ዕውቀት እና ክህሎት ሳይሰስቱ ለሌሎች አካፍለው የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የጥራት ኦዲት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ የኮሌጁ ሠራተኞች ያገኙትን የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠቅመው የግለ ግምገማ እንዲያካሂዱና ለፓይለት ኦዲቱ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበው በግለ ግምገማ ሂደቱ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ የስልጠናው ተሳታፊዎች ስልጠናው ወቅቱን የጠበቀ፣ አጭር፣ ግልጽ እና አስፈላጊ እንደነበርና በቀጣይም ከባለሥልጣኑ ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡በመጨረሻም በህክምና ትምህርት ቤት ዲን እና የኢንዶክሪን ሰርጀሪ ሰብእስፒሻሊስት ዶ/ር ወንደሰን አምታታው ለአሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የስልጠና መድረኩ ተጠናቋል፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።