“የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ስራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሠረት ተጥሏል” -ዶ/ር ድንኳና ንጉሣ- የእውቅና እና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር
ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው የእውቅና ካውንስል የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ፕሮግራም እውቅና ረቂቅ ሪፖርት የግምገማ መድረክ አካሄደ። መድረኩን በንግግር የከፈቱት በባለሥልጣኑ የእውቅና እና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንካና ንጉሣ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት የጀመረውን ስራ በተሻለ መልኩ ሊያሳካ የሚችል ስርዓት ተዘርግቶ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም ፈቃድ በመስጠት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ድንኳና የፌዴራል መንግሥት የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 515/2014 መሠረት እውቅና አሰጣጥ በዘርፍ ደረጃ እንዲደራጅ እና በምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲመራ፤መመሪያና እና ስታንዳርድ እንዲዘጋጅለት፤ በቂ የሰው ሀይልና በጀት እንዲመደብለት እና የስራ ክፍሉ በመሪ ስራ አስፈጻሚ እንዲመራ መደረጉን ገልጸዋል። የተቋማትን እና የሚያስተምሯቸው ፕሮግራሞችን በሰነድ ምርመራ እና በመስክ ምልከታ በመገምገም የጥራት ማረጋገጫ በመስጠት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ እና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ባለሥልጣኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ስራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሠረት ተጥሏል ብለዋል። በመድረኩ ማጠቃለያ ይህ ዘጠኝ አባላት ያሉት የእውቅና አሰጣጥ ካውንስል ፕሮግራም እውቅና ጥያቄ አቅርበው የሰነድ እና የመስክ ግምገማ የተድረገላቸውን የዘጠኝ ፕሮግራሞች ረቂቅ ሪፖርት በጥልቀት ገምግሞ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች አቅጣጫ አስቀምጧል። የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ