የእውቅና አሰጣጥ ስርዓት ትግበራ ያለበት ደረጃ

የኢፊዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የፌዴራል መንግሥት የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 515/2014 መሠረት ቀድሞ ከነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጥራት እና አግባብነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ የአጠቃላይ ትምህርት እና የቴ/ሙ/ት/ስ ተቋማት ጥራትን እና አግባብነትን እንዲቆጣጠር የስልጣን ወሰኑን እና ተደራሽነቱ እንዲሰፋ፤ የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖረው መደረጉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተሰጠውን ትኩረት ያመልክታል። በባለሥልጣኑ ከታዩ የሪፎርም ስራዎች ውስጥ አንዱ የእውቅና አሰጣጥ ስርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው። እውቅና አሰጣጥ ማለት ፈቃድ አግኝቶ ሲሰራ ለነበረ ተቋም ወይም ፕሮግራም በባለሥልጣኑ ለተቋም ወይም ለፕሮግራም እውቅና የወጣውን የጥራት ስታንዳርድ ስለማሟላቱ በባለሥልጣኑ ወይም በወከለው አካል ተገምግሞ የሚሰጥ የጥራት ማረጋገጫ ነው፡፡ ሥራው አዲስ እንደመሆኑ መመሪያና ስታንዳርዶች የማዘጋጀት፤ በተዘጋጀ መመሪያ፣ ስታንዳርዶች እና መገምገሚያ መሳሪያዎች ዙሪያ በአካል እና በበይነ መርብ (virtual) በመታገዝ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የመስጠት ፤ የውጭ ገምጋሚ ባለሙያ የማሰልጠን ፤ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን የመቀመር፤ የእውቅና አሰጣጥ ካውንስል የማቋቋም፤ የእውቅና አሰጣጥ ስርዓትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ለአብነት ያህል ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና የህክምናና ጤና ሳይንስ ሙያ ማህበራት ጋር ስምምነት መፈጸሙ ፤ የፕሮግራም እውቅና ለጠየቁ ተቋማት የውጭ ገምጋሚዎችን በመላክ ዴስክ ሪቪው እና ዶክመንት ስተዲ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በተቋማት ጥያቄ መሰረት የቀረቡ ሰነዶች ተመርምረው ለመስክ ግምገማ ብቁ መሆናቸውን ተገምግመው በወጣው መርሃ-ግብር መሰረት በተቋማት በመገኘት የመስክ ግምገማ ተደርጓል፤ የመስክ ግምገማው ዋነኛው አላማ ተቋማት ባስገቡት ሰነድ ላይ የተሟሉትን ጉዳዮች ስታንዳርዱ በሚጠይቀው መሰረት መኖር አለመኖራቸውን ማረጋገጥ ነው። ይህን መነሻ አድርጎ የመስክ ግምገማ ሪፖርት ተዘጋጅቶ ለእውቅና አሰጣጥ የስራ ክፍል የቀረበ ሲሆን በቀጣይ በእውቅና አሰጣጥ መመሪያ መሰረት የተዋቀረው የእውቅና ካውንስል ተሰብስቦ ውሳኔ የሚያስተላልፍ ይሆናል። በአጠቃላይ ባለሥልጣኑ በዘርፉ እየተከናወኑ ላሉ ሌሎች የሪፎርም ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት፤ ተቋማት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር ራሳቸውን እንዲገመግሙና ቀጣይ ስራቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ ለማድረግ፣ በአመለካከት በክህሎት እና በእውቀት የጎለበቱ ምሩቃንን ለማፍራት፤ቀጣሪ ተቋማት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ተማሪዎች ከውጪ ሀገራትም ጭምር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲማሩ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ለማድረግ፤ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ምሩቃን ላይ ያለው የህብረተሰቡን አመኔታ ለማሳደግ፤ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና የመፈጸም አቅምን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ የኢፊዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ