ባለስልጣኑ በሚሽከን ኮሌጅ ላይ አስፈላጊ የህግ ማስከበር እርምጃ እንዲወሰድበት አሳወቀ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁሉም ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤቶች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ጽ/ቤት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ ሚሽከን ኮሌጅ ከባለስልጣኑ የተወሰነበትን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ተሰማርቶ ዜጎች ላይ ሁለንተናዊ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠብ እና የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም እና አስፈላጊ የህግ ማስከበር እርምጃ እንዲወሰድበት በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስቧል። ባለስልጣኑ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር መሰረት በማድረግ ሚሽከን ኮሌጅ በዋና ማዕከሉ አዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በባሌ ሮቤ፣ በሀዋሳ፣ በአርባምንጭ፣ በሳውላ፣ በወላይ ታሶዶ፣ በጋምቤላ፣ በጊምቢ፣ በጅማ፣ በሆሳዕና፣ በነቀምቴ፣ በቴፒ፣ በጀግጅጋ፣ በቻግኒ እና በባህር ዳር የቅርንጫፍ ማዕከላት በቅድመ ምረቃ ደረጃ ከሀምሌ 2004 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም ፈቃድ ባገኘባቸው ከተሞች እና የትምህርት መስኮች በርቀት መርሀ ግብር ሲያስተምር የቆየ ቢሆንም በፈፀመው የህግ ጥሰት ምክንያት ማስተማሩን አንዲያቋርጥ ተደርጎ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ የተቀበላቸውን ተማሪዎች እንዲያስጨርስና በህጋዊ አግባብ የተመረቁ ተማሪዎችን መረጃ ፈቃድ ወዳለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲያዘዋወርና ለባለስልጣኑ ሪፖርት እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ኮሌጁን መጠየቁን አስታውሶ ሆኖም ተቋሙ የተላለፈበትን ውሳኔ ተግባራዊ እያደረገ ባለመሆኑ በደብዳቤው የተገለጹ የመንግስት አካላት በተቋሙ ላይ አስፈላጊውን የህግ ማስከበር እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል፡፡ የኢፊዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።