የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለሥልጣኑን የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገመገመ

ባለሥልጣኑ የተጣለበትን የትምህርትን ጥራትና አግባብነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዲወጣ ውጤታማ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ገለፁ፡፡ የባለሥልጣኑ የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው በበኩላቸው ባለፉት 6 ወራት በተሰሩ ስራዎች የአመለካከት ለውጥ መምጣቱን የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቀመጠውን አነስተኛ የጥራት መመዘኛ ለማሟላት ጥረት እንዲያደርጉ ማነሳሳቱን ገልፀዋል፡፡ ከቋሚ ኮሚቴው የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ተልእኮን ከማሳካት ፤ የትምህርትና ስልጠና ጥራትና አግባብነትን በላቀ ደረጃ ከማስጠበቅ፤በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ከመቅረፍ ፤ ብልሹ አሰራርን ከመከላከል እና ከማስወገድ እንዲሁም ባለሥልጣኑ ብቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማስቻል አንፃር ለተነሱ ጥያቄዎች በኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው፤የእውቅናና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ፤በተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ እና የጥራት ኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ እና በተቋማት ቁጥጥር ኢንስፔክሽን እና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ኤሮ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር በተልሄም ላቀው በቀረበው የቋሚ ኮሚቴው ግብረመልስ እንደተመላከተው የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ እና የአቻ ግመታ ሥራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑ ዘመኑን የዋጀ እና የዜጎችን እንግልት ያስቀረ መሆኑ ተገልጿል፡፡በዳግም ምዝገባ ስራ እየተሳተፉ ለሚገኙ ሰራተኞች ስልጠና መሰጠቱም በመልካም ጎን የሚጠቀስ መሆንን ተናግረዋል፡፡ በዳግም ምዝገባ ሂደት ያላለፉትን ተቋማት ከፈቃድ ስርዓቱ እንዲውጡ መደረጉ እንዲሁም ባለሥልጣኑ የሂሳብ ነቀፌታ የሌለበት የኦዲት አስተያየት/Clear Opinion/ እዉቅና ከገንዘብ ሚኒስቴር ማግኘቱ በመልካም ጎን የሚጠቀሱ ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ፈቃድ የተሰጣቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምዝገባ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፤የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የጥራት ኦዴት አለመሰራቱ፤ባለሥልጣኑ የአህጉር አቀፍ እና የዓለምአቀፍ የጥራት ፎረም አባል አለመሆኑ ፤የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ስራቸውን እያከናወኑ ስለመሆኑ ክትትል ለማድረግ ታቅዶ አለመከናወኑ በደካማ ጎን የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የክትትል እና የቁጥጥር ስራው በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት አግባብነትን ከማረጋገጥ አንጻር ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ፤አጋርነትና ትስስርን በማጠናከር በትብብር መስራት ፤ ከጥራት ማስጠበቅ እና ከእውቅና አሰጣጥ ስራዎች ጋር በተያያዘ የጊዜ ገደብ አስቀምጦ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ፤ከዓለም አቀፍ እና ማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘም የትምህርት ስርዓቱ ከሀገሪቱን እሴት ጋር የማይጣረስ መሆንእንዳለበት ፤ባለስልጣኑ በአመራርና በአደረጃጀት ሊጠናከር እንደሚገባ እና የባለሥልጣኑ የውስጥ ጥራት ኦዴት ሊጠናከር እንደሚገባ እንዲሁም ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘም የድጋፍ ፤ የክትትል እና እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ