ባለስልጣኑ በገንዘብ ሚኒስቴር የእዉቅና እና የምስጋና ደብዳቤ ተሰጠው

የኢፌዲሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በ2015 በጀት ዓመት ሂሳብ ነቀፌታ የሌለበት የኦዲት አስተያየት/Clear Opinion/ እና በ2016 በጀት ዓመት ለኢንስፔክሽን መምሪያ መቅረብ የሚገባቸዉ የተለያዩ ሪፖርቶችና ግብረ መልስ አፈጻጸም ዉጤት በመመሪያዉ መሠረት በወቅቱ በማቅረቡ በገንዘብ ሚኒስቴር የእዉቅና እና የምስጋና ደብዳቤ ከተሰጣቸዉ 12 የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ አንዱ ሆነ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር የተሻለ የኦዲት አፈጻጸም ላስመዘገቡ 12 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የዕውቅና ሽልማት ሰጠ መስከረም 23/2017 ዓ.ም - የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ በፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በሚከናወኑ የውስጥ ኦዲት ስራዎች እና በፌዴራል የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2015 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት አፈጻጸም ላይ ለመወያየት ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ 12 ለሚሆኑ የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የእውቅና ሽልማት ተሰጠ፡፡ የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ ለፌዴራል ተቋማት የፋይናንስ እና የውስጥ ኦዲት ኃላፊዎች የተዘጋጀውን የምክክር መድረክ ሲከፍቱ እንደገለጹት ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ በሚኒስቴሩ እና በባለድርሻ አካላት በተከናወኑ ስራዎች መሻሻሎች እየታዩ የመጡ ሲሆን በ2015 በጀት ዓመት ነቀፌታ የሌለው የኦዲት አስተያየት ያገኙ ተቋማትን 53 በመቶ ለማድረስ ተችሏል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን የአሰራር ስርዓት በማዘመን ውጤታማ፣ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ ህጎችን በማውጣት፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠትና ክትትል በማድረግ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ሚንስትሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ በሚኒስቴሩ የኢንስፔክሽን መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ አባይነሽ ተሾመ በበኩላቸው በሚኒስቴሩ እና በባለድርሻ አካላት በተከናወኑ ተከታታይነት ያላቸው ስራዎች የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በተለይም ከአሁን በፊት የኦዲት ችግር ይስተዋልባቸው የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች በዕቅድ የመመራትና በወቅቱ ሪፖርት የማድረግ አፈጻጸም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በ2015 በጀት ዓመት ነቀፌታ የሌለበት የኦዲት ሪፖርት በማስመዝገባቸው የእውቅና ሽልማት ከተሰጣቸው የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች መካከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት፣ የሠላም ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽ/ቤት፣ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት‹ የፖሊሲ ጥናት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፣ ጅንካ ዩኒቭርሲቲ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል፡፡ በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ