የዓለም አቀፍ ፣የማህበረሰብ፣ የበጎ አድራጎት እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች የፈቃድ እና የፈቃድ እድሳት እና ተያያዥ ሥራዎች ወደ ባለስልጣኑ መዘዋወሩን ለማሳወቅ የሚያስችል የውይይት እና የትውውቅ መድረክ ተካሄደ
የዓለም አቀፍ ፣የማህበረሰብ፣ የበጎ አድራጎት እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ባለቤቶች እና ህጋዊ ወኪሎቻቸው በተገኙበት ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ የፈቃድ እና የፈቃድ እድሳት ሥራዎች ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መዘዋወሩን እና በቀጣይ ስለሚኖረው የሥራ ግንኙነት ለመወያየት እና ለመተዋወቅ የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ። በውይይት መድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በባለሥልጣኑ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና አጠቃላይ ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መቅደስ ደረሰ የዓለም አቀፍ ፣የማህበረሰብ፣ የበጎ አድራጎት እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች የፈቃድ እና የፈቃድ እድሳት ሥራዎች ቀደም ሲል በትምህርት ሚኒስቴር ይሠሩ እንደነበር ገልጸው ፤የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀፅ 60(1) በሌላ ስያሜ ትምህርት እና ስልጠና ባለሥልጣን ተብሎ ሲቋቋም እና በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 515/2014 አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ መሠረት አገልግሎቱ ወደ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ መዛወሩን አስታውቀዋል፡፡ በባለሥልጣኑ የተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ እና የጥራት ኦዲት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በባለስልጣኑ እና በትምህርት ሚኒስቴር መካከል ሲደረግ ስለነበረው የሥራ ርክክብ ሂደት እና በቀጣይ ስለሚኖሩ የሥራ ግንኙነቶች ተናግረዋል፡፡ ለውይይት መነሻ የሚሆን ገለጻ በወ/ሮ መቅደስ የቀረበ ሲሆን በገለጻቸውም የዓለም አቀፍ ፣የማህበረሰብ፣ የበጎ አድራጎት እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ፈቃድ ለመስጠት ባለሥልጣኑ ስላለው ህጋዊ መሠረት፤ ስለ ዓለም አቀፍ፤ የማህበረስ፤የበጎ አድራጎት፤ለትርፍ ያልተቋቋሙ ት/ቤቶች ፈቃድ እና የፈቃድ እድሳት መመሪያ 992/2016 ይዘት ፤የወላጅ፣ተማዎች፣መምህራን ህብረት መመሪያ 993/2016 ይዘት፤ ፈቃድ እና የፈቃድ እድሳት ሥራ ከትምህርት ሚኒስቴር ወደ ባለሥልጣኑ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ ስለተሠሩ ሥራዎች፤ በቀጣይ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር በጋራ ለመስራት ስለ የሚያስችሉ የሥራ አቅጣዎች እና በባለስልጣኑ ስለ ተዘጋጁ የአሰራር ሰነዶች በሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የቀረበውን የውይይት መነሻ ሀሳብ የያዘ ገለጻ መሠረት በማድረግ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በባለሥልጣኑ የተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ እና የጥራት ኦዲት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ እና በወ/ሮ መቅደስ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡ በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ
