የተቋም፣ፕሮግራም እና የካምፓስ ምንነት ፤ ከትምህርት ሴክተር ለመውጣት የሚፈልጉ ሊያሟሉ የመውጫ መስፈርቶች እና የመውጫ አሰራር ስርዓት፡-

በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ፤ በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 መሠረት፡- ተቋም ማለት፡- የመንግስት ወይም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው:: የመንግስት ተቋም ማለት ፡- እንደ አግባብነቱ በጀት በፌዴራል ወይም በክልል መንግስት የሚመደብለት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው:: የግል ተቋም ማለት ፡- በአንድ ግለሰብ ወይም ከአንድ በላይ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ባለቤትነት ወይም ዓላማው ለትርፍ ባልሆነ ማኅበራት ወይም በህብረት ሥራ ማኅበራት ወይም በንግድ ማኅበርነት የተመሠረተ ወይም በውጭ ሀገር የተመሠረተና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው፡፡ ካምፓስ ማለት፡- በዩኒቨርሲቲ ወይም በኮሌጅ ባለቤትነት ወይም ቁጥጥር የሚደረግበት ሆኖ ትምህርታዊና አስተዳደራዊ ስራዎች የሚከወኑበት ከባቢ/ጊቢ ማለት ነው። ፕሮግራም ማለት፡- በባለሥልጣን መ/ቤቱ ፈቃድ በተሰጠው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚሰጥ የትምህርት መስክ ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፈቃድ እና ፈቃድ እድሳት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 988/ 2016 መሠረት የተቋም፣ፕሮግራም እና የካምፓስ የመውጫ አሰራር ስርዓት፡-  ማንኛውም ተቋም በራሱ ተነሳሽነት ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ያገኘበትን ፕሮግራም ወይም ስልጠና መዝጋት የሚችለው ተቀባይነት ባለው መነሻ ምክንያት መማር ማስተማሩን ማስቀጠል በማይችልበት ሁኔታ ለባለሥልጣኑ ከ6 ወር በፊት በማመልከት ባለሥልጣኑ ያወጣውን ዝርዝር መስፈርት ካሟላ እና ሲፈቀድለት ብቻ ሊወጣ ይችላል፤ እና  በጥራት መጓደል ወይም በህግ ጥሰት ምክንያት ፈቃድ ያገኘበትን ወይም ያገኘባቸውን ፕሮግራም(ሞች) ወይም ስልጠና(ዎች) እንዲዘጋ በባለሥልጣኑ የታዘዘ ተቋም እየተማሩ ያለ ተማሪዎችን ፈቃድ ወዳለው ሌላ ተቋም ተማሪዎቹ በመረጡት እና በባለሥልጣኑ በሚወሰን የጊዜ ገደብ ውስጥ በማዘዋወር እና የሂደቱን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ለባለሥልጣኑ ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ በባንክ ካስያዘው አምስት መቶ ሺህ ብር ላይ ለዚሁ ዓላማ እንዲውል ይደረጋል። ከትምህርት ሴክተር ለመውጣት የሚፈልጉት ተቋማት ፣ፕሮግራሞች እና ካምፓሶች የሚከተሉትን የመውጫ መስፈርቶች ሊያሟሉ ይገባለ፡-  ኦሪጅናል የፈቃድ ሰርቲፊኬት መመለስ፤  ፈቃድ ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ፈቃድ በነበረው ወቅት የመግቢያ መስፈርቱን አሟልተው በተቋሙ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎችን ስም ዝርዝር እና የትምህርት ማስረጃ እንደሚከተለው ማስረከብ፤  ተማሪዎቹ ሲመዘገቡ በመግቢያነት ያስያዙት የትምህርት ማስረጃ፤  ተማሪዎቹ የመለሱት መታወቂያ ካርድ፤  የተማሪዎቹ ስም ዝርዝር፤  ተማሪዎቹ የተመረቁበት/የተማሩበት ፕሮግራም ስም፣ ደረጃ እና ሞዳሊቲ፤  ተማሪዎቹ በተቋሙ የተመዘገቡበት ዓመተ ምህረት፤  ተማሪዎቹ በተቋሙ ትምህርታቸውን የጨረሱበት ዓመተ ምህረት፤ .  የተማሪዎቹ የመጨረሻ ሴሚስተር ኮሙሌቲቭ ውጤት፤  የሴኔት/አካዳሚክ ኮሚሽን የተመራቂ ተማሪዎች ቃለ-ጉባኤ፤ (ወቅቱን ጠብቆ የተዘጋጀ፤ በሶፍትና በሀርድ ኮፒ የሚቀርብ)  የተማሪዎችን ስም ዝርዝር እና የትምህርት ማስረጃ ያስረከበበትን ቀሪ የውል ስምምነት ሰነድ እና ቃለ ጉባኤ ማስገባት፤  ተቋሙ ከምንም ዓይነት የመንግስት እዳ ነጻ ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ፤  የሚጠበቅበትን የስራ ግብር፣ የቤት ኪራይ፣ የስልክ፤ የመብራት፤ የውሀ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ ከፍሎ ያጠናቀቀ ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ፤ እና  ከወንጀል ነጻ ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ፡፡ የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን