በመረጃ ነጻነት አዋጅ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
በመረጃ ነጻነት አዋጅ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ ------------------------------------------------------------------- መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም በባለሥልጣኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመረጃ ነጻነት አዋጅ፤አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት ላይ የተሰጠውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በንግግር የከፈቱት በኢፊዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታምሩ መስፍን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኔኬሽን የሥራ ክፍል አቅዶ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱ እንደዚህ ዓይነት ግንዛቤ ለመፍጠር እና አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን የባለሥልጣኑን የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኔኬሽን ስራ ማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙትና ኮሙዩኔኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ማርታ አድማሱ በበኩላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተዘጋጀው የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኔኬሽን የሥራ ክፍል በባለሥልጣኑ ከሚገኙ ሁሉም የሥራ ክፍሎች የሚገኙ መረጃዎችን አቀናጅቶ እና አደራጅቶ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንዲሁም በባለሥልጣኑ በሚደረጉ የዕለት ተእለት የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚኖሩ የመረጃ ልውውጦች የመረጃ ነጻነት አዋጅ ፤አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስትን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ የማስቻል ግንዛቤን ለማሳደግ እና አቅምን ለማጎልበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት በኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ህግ ማስተግበር የዴስክ ኃላፊ አቶ ታደሰ ጣሰው የመረጃ ነጻነት የሰዎችን የመናገርና ሃሳብን የመግለጽ መብት፤ የሰዎችን መረጃ የመፈለግ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብትን ያካተተ መሆኑን ገልጸው የመረጃ ነጻነት ህግ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያለውን የዜጎች መረጃ የማግኘት መብትን ተግባራዊ ማድረግ ዋና ዓላማ አድርጎ የተደነገገ ግልፅነትና ተጠያቂነትን እንዲሰፍን፤በዕቅድ ለመመራትና ለውጤታማነት፤ለመልካም አገልግሎት አሰጣጥ፤የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጠናከር፤የኢኮኖሚ እድገትን ለማጠናከር፤ለፍትህና ሌሎች የዜጎች ጥቅሞችንለማስከበር በር የሚከፍቱ ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቶ ታደሰ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት ሕገ-መንግሥት፣ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ የውጭ ሀገራት ተሞክሮ እና የሀገራችን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው መረጃ ማለት ፈጣሪው መንግስት ወይም ከመንግስት ውጪ በሆነ አካል በማናቸውም ጊዜ የተፈጠረ፤ በማናቸውም ዓይነት የተቀናበረ መዝገብ፣ኤሌክትሮኒክ ሪኮርድ፣ ወዘተ ማንኛውም ዓይነት ሰነድ ማለት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በስልጠና መድረኩ ላይ የመረጃ ነፃነት መሠረታዊ ፅንሰ-ሀሳብ፤የልዩ ልዩ ሀገራት ተሞክሮዎችና ዓለም አቀፍ ገጽታ፤የመረጃ ነፃነት ህግ (አዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት) መነሻና ይዘት፤የመረጃ ነፃነት መርሆዎችና ጠቀሜታዎች እና የመረጃ ነፃነት ዋና ዋና ድንጋጌዎችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እና ገለጻ በአሰልጣኙ አቶ ታደሰ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በአሰልጣኙ አቶ ታደሰ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና መድረኩ ተጠናቋል፡፡ የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ
