ባለሥልጣኑ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድ ጋይድላይን ላይ በበየነ መረብ ወርክሾፕ አካሄደ

የኢፊዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድ ጋይድላይን ላይ ህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም በየካቲት 12 ሆስፒታል ሚዲካል ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ቤት በበየነ መረብ ባካሄደው ወርክሾፕ ላይ የጀርመን አካዳሚክ ኤክስቼንጅ ሰርቪስ (DAAD) ተወካይ እና የትብብር፣ የፓርትነርሽፕ ፕሮግራሞች፣ የቀድሞ ተማሪዎች ፕሮጀክቶችና የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር ከፍተኛ የዴስክ ኦፊሰር ወ/ሮ ሳራ ላንግ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የኘሮጀክቱ ዓላማ የፓን አፍሪካን የጥራት አጠባበቅ ማእቀፍ ለከፍተኛ ትምህርት ጥራት አጠባበቅ ያለውን ፋይዳ ማስተዋወቅና የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተስማሙበትን የጋራ ስታንድርድ እንዲቀጠሙ ማበረታታት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ኦፊሰር ወ/ሮ ሳራ ቀጠናዊ ትስስር ለመፍጠር፣ የተማሪዎችን አህጉር አቀፍ እንቅስቃሴና የብቃት ማዕቀፍ እውቅና ለመስጠት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑንና የአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድና ጋይድላይን (ASG-QA) ለማስፈጸም ወሳኝ መሣሪያ መሆኑን እና በዚህ ኘሮጀክት የአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንድርድና ጋይድላይንን ከሀገራችና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመን ለመጠቀም የሚያስችል እውቀት የሚሰጠን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጀመርመን አካዳሚክ ኤክስቼንጅ ሰርቪስ(DAAD) የመቶ ዓመት ታሪክ ያለው ፤ ተልዕኮው የከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋትና የተማሪዎችና የምርምር ባለሙያዎችን ልውውጥ ማበረታታት መሆኑን እና HAQAA (Harmonization of African Higher Education Quality Assurance and Accreditation) የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት፣ በጀርመን አካዳሚክ ኤክስቼንጅ ሰርቪስ (DAAD)፣ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከተባበሩ አጋር አካላት ጋር በጋራ የተመሠረ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። በባለሥልጣኑ የስታንዳርዳይዜሽንና የብቃት ማረጋገጫ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ሀብታሙ ተሾመ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እያድረጉ ላሉት ድጋፍ እና ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ሀብታሙ የጥራት ማረጋገጫ ስርዓቶችን ለማናበብ እና ለማጠናከር የሚደረገው የጋራ ጥረት አህጉራዊ የጥራት ባህል ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው ሀገራችን በጥራትና በተዛማጅነት ላይ ትኩረት በማድረግ አጠቃላይ የትምህርት እና የሥልጠና ማሻሻያ እያደረገች በመሆኑ የአፍሪካ የጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድና ጋይድላይን (ASG-QA) የአፍሪካ ባለቤትነት ያለው የአህጉራችንን እውነታዎች ይዞ የተገነባ እና በዓለም አቀፍ ልምዶች ላይ የተመሠረተ ፣ ከአህጉራዊ ስታንዳርዶች ጋር በማጣጣም ለአካዳሚክ ተዓማኒነት በሮችን የከፈተ መሆኑን ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት የእውቅና አሰጣጥ ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ስርጉት ሽመልስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የእውቅና(accreditation) ስታንዳርዶች እና ስታንዳርዶቹ ሲዘጋጁ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሠረት ባደረገ የእውቅና ግምገማ ፕሮሲጀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብነት ተሾመ የአፍሪካ ጥራት አጠባበቅ ስታንዳርድና ጋይድላይን (ASG-QA) ታሪካዉ ዳራ፣ የኢትዬጵያ የእውቅና (Accreditation) ስታንዳርድ ከአፍሪካ ጥራት ማስጠበቅ ስታንዳርድና ጋይድላይን (ASG-QA) ጋር ያለውን ትስስርና ልዩነት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱም በአፍሪካ ደረጃ ስታንዳርድ መኖሩና የሀገራችን ስታንዳርድ ከአህጉር አንፃር እንዲጣጣም ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች እንደሆነ፤ እንደ ጀማሪ የእውቅና አሰጣጥም ሆነ የጥራት ኦዲት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች ዳግም ምዝገባ ዝርዝር የመገምገሚ መስፈርትና ውጤት አመላካች መያዙ ለተቋማት ጥራት ማስጠበቅ ጠቃሚ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዎች አቅማቸውን እየገነቡ ሲመጡ ለቀቅ የማድረግ ስራ ታሳቢ መደረግ አለበት የሚሉት ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ይገኙበትል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የመዝጊያ መልእክት ያስተላለፉት የጥራት ኦዲት መሪ ስራ አስፈፃሚ እና የተቀናጀ የአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና እውቅና ኢኒሼቲቭ (HAQAA3) አምባሳደር ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ እንደ ሀገር ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራሞች የዓለም አቅፍ እውቅና ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግ የተቀመጠ መሆኑ፣ ሀገር አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ ማህቀፍ( ENQF) ለመተግበር የሚያስችል ደንብ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስር መፍጠር የጋራ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ።