በአካዳሚክ የጥራት ኦዲት የህግ ማዕቀፍ እና የአሰራር ስርዓት ሰነዶች ዙሪያ ከመንግስትና ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ከፊደራል እና ከክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ለተውጣጡ የውጭ ኦዲተሮች ስልጠና ተሰጠ
በኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጣና ባለስልጣን የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ በአካዳሚክ የጥራት ኦዲት የህግ ማዕቀፍ እና የአሰራር ስርዓት ሰነዶች ዙሪያ ከመንግስትና ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ ከፊደራል እና ከክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከተውጣጡ የውጭ አካዳሚክ ጥራት ኦዲተሮች ጋር ከጥቅምት 10 እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ስልጠና ተሰጠ፡፡ የባለስልጣኑ የጥራት ኦዲት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ የስልጠናው ዓላማ የኢፌድሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የከፍተኛ ትምህርትና እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ስልጠና፤ ጥናትና ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ፤እንዲሁም ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ተመራቂዎችን እንዲያፈሩ ለማስቻል ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የአካዳሚክ ጥራት ኦዲት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መሪ ስራ አስፈፃሚዋ የተሻሻለው የአካዳሚክ ጥራት ኦዲት አሰራር የተቋማትን የውስጥ ጥራት ማረጋገጫ ስርዓት ውጤታማነትን ለመገምገም ፣ ሀገራዊ ግብን ፣ የባለድርሻ አካላት ፍላጎት እና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማጣጣም የተቀረፀ መሆኑን ገልፀው የጥራት ኦዲተሮች የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጥ ሥርዓት ውስጥ የጀርባ አጥንት በመሆናቸው የውጪ ኦዲተሮች በኦዲት ሂደት ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆነ የጥናትና ምርምር ስራ የሚሳተፉ፣ ስራቸው ስታንዳርድ መጠበቁን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ውስብስብ አካዳሚያዊ፣ አስተዳደራዊ እና ተቋማዊ ሥርዓቶችን በከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነት መገምገምና ውሳኔ መስጠት የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በስልጠናው ላይ በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ኦዲት ባለሙያዎች እና የዴስክ ኃላፊዎች እና መሪ ሥራ አስፈጻሚ የተለያየ ይዘት ያላቸው ገለፃዎችን አቅርበዋል፡፡ የከፍተኛና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና መመሪያ ወ/ሮ ትዕግስት ኃይለስላሴ፣ የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ስታንዳርዶች በወ/ሮ ውብነሽ ሽፈራው፤ የጥራት ኦዲት ፕሮሲጀር በአቶ ነዋይ ሙሉ ፤ የቅድመ ኦዲት በአቶ ጋሻውጠና አዳፍሬ፤ የጥራት ኦዲት ሪፖርት አጻጻፍ በአቶ ሁርጂ ሙሉጌታ፤ የጥራት ማጎልበቻ እቅድ በአቶ ቦንሳ ዋቅጋሪ ፤የክትትል ኦዲት በአቶ አኑዋር እንድሪስ እና የግለ ግምገማ አዘገጃጀት በባለሥልጣኑ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የዴስክ ኃላፊ በሆኑት በአቶ እሸቱ እዬብ እንዲሁም የኦዲተሮች ምልመላና መረጣ የከፍተኛ ትምህርት የዴስክ ኃላፊ በሆኑት በአቶ አብይ ገዛኽኝ ቀርቦ በቡድን ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ የፓይለት ኦዲት የግለግምገማ ዝግጅት ተሞክሮ በዶ/ር ባለው አረጋ እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲቲዩት ተሞክሮ በዶ/ር ሀ/ማርያም ንጉስ ቀርቧል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ ከጥራት ኦዲት አንጻር የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በተመለከተ የውይይቱ ተሳታፊዎች የመጡባቸው ተቋማት ያላቸውን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ለቀጣይ ሥራ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን እና አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት የዴስክ ኃላፊ አቶ አብይ ገዛኽኝ ስልጠናው የጥራት ኦዲተሮች የጥራት ኦዲት አሰራር ላይ የተሻለ እውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ለሰልጣኞች የተዘጋጀው የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡ የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጣና ባለስልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ
