የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርት ተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ስራዎች

በባለሥልጣኑ ላይ በተደረገው የአደረጃጀት፣ የሰው ሀይል፣ የበጀት እና የመዋቅራዊ ለውጥ መሠረት ከተደራጁ አዳዲስ የስራ ክፍሎች መካከል የተቋማት ክትትልና ቁጥጥር የሥራ ክፍል አንዱ ነው፡፡ የተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ማለት ተቋማት በክትትልና ቁጥጥር ወቅት የተገኙ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ የተቀመጠውን የጥራት መስፈርቶች አጓድለው ሲገኙ የሚወሰድ የማስተካከያ እርምጃ ነው፡፡ የሥራ ክፍሉ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል የተቋማት ድንገተኛ ጉብኝት አንዱ ነው፡፡የትምህርትና ሥልጠና ጥራትን በዘላቂነት የሚጎዱ ተግባራት ስለመኖራቸው ለማረጋገጥ ጉብኝት ለማድረግ መደበኛ መረሐ ግብር መያዝ ሳያስፈልግ በተቋማት በአካል በመገኘት ወይም ባለሥልጣኑ በሚደርሰው መረጃ መሠረት የሚደረግ የመስክ ጉብኝት ወይም ምልከታ ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተከለከሉ እና የእርምት እርምጃ የሚያስከትሉ ተግባራት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳያገኝ ሲያስተምር የተገኘ አዲስ ተቋም፤ፈቃድ ባልተገኘበት ካምፓስ ወይም ቅርንጫፍ ትምህርት ሲሰጥ የተገኘ ተቋም፤ባልተፈቀደ የትምህርት-መስክ እና መረሀ-ግብር ትምህርት እየሰጠ የተገኘ ተቋም፣ ፍቃድ ሳያድስ ስያስተምር የተገኘ ተቋም፣ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳያገኝ የህንጻ ለውጥ ያደረገ ተቋም፤ የአጫጭር ስልጠና እና የማማከር አገልግሎት ፈቃድ ሳይሰጣቸው የሚሰሩ ተቋማት ወይም የሙያ ማህበራት፣ በባለሥልጣኑ ከተሰጠው የደረጃ ስያሜ ውጪ ሌላ የደረጃ ስያሜ ሲጠቀም የተገኘ ተቋም፣ አሳሳች ማስታወቂያ ያሰራጨ ተቋም፤ የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ መስፈርት ያላሟሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር የተገኘ ተቋም፣ በባለሥልጣኑ ተገምግሞ ያገኘውን ስርዓተ ትምህርት ሳይከተል ትምህርት የሰጠ ተቋም፣ የመምህራንን ቁጥር እና ደረጃ አጓድሎና ቀይሮ የተገኘ ተቋም፣ በባለስልጣኑ ከተፈቀደው ቁጥር በላይ መዝግቦ ሲያስተምር የተገኘ ተቋም፣ የተማሪ መረጃ አያያዝ፣ አጠባበቅና አላላክ፣ ባለሥልጣኑ የተሰጠውን የፈቃድ እና ፈቃድ እድሳት ደብዳቤ በግልጽ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በሚታይ ሁኔታ ያለጠፈ ወይም ያላሳወቀ ተቋም እና ግብአቶችን አጓድሎ ወይም ከተቋም ወደ ሌላ ተቋም ወይም ካምፓስ አዛውሮ የተገኘ ተቋም፤ሐሰተኛ ሰነዶች እና ትክክለኛ ያልሆኑ ማስረጃዎች ትክክለኛ አድርጎ ማቅረብ ናቸው፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የተከለከሉ እና የእርምት እርምጃ የሚያስከትሉ ተግባራት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ፈቃድ ባልተገኘበት ተቋም ስልጠና መስጠት፤ባልተፈቀደለት የሥልጠና መስክ ስልጠና እየሰጠ የተገኘ ተቋም፤ ፈቃድ ሳያድስ ሲያስተምር የተገኘ ተቋም፤ በባለሥልጣኑ ከተሰጠው የደረጃ ስያሜ ውጪ ሌላ የደረጃ ስያሜ ሲጠቀም የተገኘ ተቋም በሀገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ከሚያዘጋጀው የሙያ ደረጃ እና ስርዓት ትምህርቱ ወጭ ሲያሰለጥን የተገኘ ተቋም፤የሥልጠና መስክ አሰልጣኞች አዛውሮ ወይም ቀይሮ ሲገኝ፤ ስልጣን ባለው አካል የወጡ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መግቢያ መስፈርት ሰልጣኞችን ተቀብሎ ስልጠና የሰጠ ተቋም፤ከተፈቀደለት ሰልጣኝ ቁጥር በላይ መዝግቦ ሲያሰለጥን የተገኘ ተቋም፣ የተማሪ መረጃ አያያዝ፣ አጠባበቅና አላላክ፤ባለሥልጣኑ የተሰጠውን የፈቃድ እና ፈቃድ እድሳት ደብዳቤ በግልጽ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በሚታይ ሁኔታ ያለጠፈ ወይም ያላሳወቀ ተቋም እና ባለሥልጣኑ የተሰጠውን የፈቃድ እና ፈቃድ እድሳት ደብዳቤ በግልጽ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በሚታይ ሁኔታ ያለጠፈ ወይም ያላሳወቀ ተቋም፤ሐሰተኛ ሰነዶች እና ትክክለኛ አድርጎ ማቅረብ ናቸው፡፡ የተቋማት ክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን ለማሻሻል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ በተሰጣቸው አግባብ መሰረት ስራቸውን እያከናወኑ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ በሰነድ ምርመራና ድንገተኛ የመስክ ምልከታ በማድረግ የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ ከከፍተኛ ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ እና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ እና አቻ ግመታ የሥራ ክፍሎች የሚደርሱትን መረጃዎች በመመርኮዝ የክትትል እና የቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር የማስተካከያ እርምት እርምጃ በመውሰድ ባለሥልጣኑ የተጣለበትን የትምህርትና ስልጠና ጥራት የማረጋገጥ ተልእኮ እንዲወጣ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ የኢፊዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ