በ7 ዓመቱ የለውጥ ፍሬዎች ላይ ውይይት ተካሄደ

የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ባለፉት 7 ዓመታት በተገኙ የለውጥ ፍሬዎች ላይ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ተወያዩ፡፡ በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ባለፉት 7 ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ እና የተገኙ ውጤቶችን የሚመለከት ጽሁፍ የተቋማት ቁጥጥር ኢንስፔክሽንና የትምህርት ማስተጃ ማረጋገጫ ም/ዋና ዳይሬክተር በአቶ ቢኒያም ኤሮ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው፣ እንዲሁም የተቋማት እና ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዱንካና ኑጉሳ በጉዳዩ ዙሪያ ከሰራተኛው ጋር ተወያይተዋል፡፡ የውይይቱ አላማ ሰራተኞች የተገኙ ሀገራዊ መልካም ውጤቶችን መሰረት በማድረግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ ጽሁፉን ያቀረቡት አቶ ቢኒያም ገልጸዋል። የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎች እና ተስፋዎች በሚል ርዕስ በተካሄደው የ7ኛ ዓመት አከባበር ተሳታፊ የሆኑ የባለሥልጣኑ ሰራተኞች ላነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከፍተኛ አመራሮቹ ምላሽ ሰጥተዋል። በማጠቃለያ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ሁሉም የልማት ዘርፎች የሚፈልጉትን የሰው ሀይል ተቋማት በጥራት እንዲያፈሩ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ኃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። በፊስቡክ -https://www.facebook.com/FDRE.ETA በትዊተር- https://twitter.com/FDRE_ETA በቴሌግራም -https://t.me/FDRE_ETA በዌብሳይት Www. neta.gov.et ይከታተሉ